“ማንም እንዲያስፈራራን አንፈቅድም” - ፑቲን
የምዕራባውያን “እብሪተኝነት” ቢቀጥልም ሩሲያ አለማቀፍ ግጭትን ለማስቀረት የትኛውንም እርምጃ ትወስዳለች ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ
ሩሲያ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ናዚ ጀርመንን ያሸነፈችበትን የድል በዓል አክብራለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን አለማቀፍ ግጭት እንዲቀሰቀስ እያደረጉ ነው ሲሉ ወቀሱ።
ፕሬዝዳንቱ 79ኛው የሩሲያ የድል በዓል ሲከበር ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአለማችን ግዙፍ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤቷን ሀገር “ማንም ሊያስፈራራት አይችልም” ብለዋል።
ፑቲን በንግግራቸው “እብሪተኛ” ሲሉ የገለጿቸው ምዕራባውያን ምሁራን ሶቪየት ህብረት በሁለተኛው የአለም ጦርነት የናዚ ጀርመን ጦርን በማሸነፍ ረገድ የነበራትን ጉልህ ሚና ዘንግተው ሌላ የአለም ጦርነት ለመቀስቀስ እየጣሩ ነው ማለታቸውንም ሬውተርስ አስነብቧል።
ይህ የምዕራባውያኑ ፍላጎት ወደየት እንደሚያመራ እናውቃለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ሩሲያ አለማቀፍ ግጭት እንዳይከሰት የምትችለውን ሁሉ ታደርጋለች ሲሉ ተደምጠዋል።
“አለማቀፍ ግጭትን ለማስቀረት ጥረት ማድረጋቸውን ብንቀጥልም ማንም እንዲያስፈራራን ግን አንፈቅድም፤ ስትራቴጂካዊ ሃይላችን ለየትኛውም የጥቃት እርምጃ ዝግጁ ነው” ብለዋል ከቀናት በፊት ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን ቃለመሃላ የፈጸሙት ፑቲን።
በ79ኛው የድል በዓል ላይ ሩሲያ ከወትሮው ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም ወታደራዊ ትርኢት አሳይታለች ተብሏል።
ሞስኮ “በየትኛውም አለም ጥቃት ማድረስ ይችላል” የተባለውን ያርስ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሏል ለእይታ አቅርባለች።
የቤላሩስ፣ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ኩባ፣ ጊኒ ቢሳው እና ሌሎች ሀገራት መሪዎች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል።
ሩሲያ ከ18 በመቶ በላይ የዩክሬን ግዛት የተቆጣጠረችበትን ጦርነት የሚቃወሙና ለኬቭ ድጋፍ የሚያደርጉ ሀገራት በድል በዓሉ ላይ አልተገኙም።
ሩሲያ በቅርቡ በድል በዓሉ መታሰቢያ ፓርክ ውስጥ በቅርቡ በዩክሬን የማረከቻቸውን የምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች ለእይታ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።