ፑቲን “ዩክሬን በምርጫ ቀን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ትቀጣለች” ሲሉ ዛቱ
በሩሲያዋ ቤልግሮድ ክልል በዩክሬን ተፈጸመ በተባለ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሞተዋል
ፕሬዝዳንት ፑቲን “እንዲህ አይነት ጥፋቶች ያለ ቅጣት አይታለፉም” ሲሉ ተናግረዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ዩክሬን በምርጫ ቀን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ትቀጣለች” ሲሉ ዝተዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከባለፈው እርብ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም ሶስተኛ እና የመጨረሻ ቀኑ ላይ ይገኛል።
በፕሬዝዳንተዊ ምርጫው ሁለተኛ ቀን ማለትም በትናንትናው እለት በሩሲያዋ ቤልግሮድ ክልል በዩክሬን ተፈጸመ በተባለ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሞተዋል የተባለ ሲሆን፤ ይህም ሩሲያን ክፉኛ አስቆጥቷል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጥቃቱ ዙሪያ ከሩሲያ የደህንነት ምክር ቤት አባላት ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ በጉዳድ ላይም ከበድ ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ፑቲን በንግግራቸው፤ “ጠላት በቤልግሮድ ክልል በአራት አቅጣጫዎች እንዲሁም በኩርስክ ክልል በአንድ አቅጣጫ የሽብር ጥቃት ከፍቶ ነበር” ብለዋል።
“ለጥቃቱም ጠላት 2 ሺህ 500 ወታደሮችን፣ 35 ታንኮችን እንዲሁም 40 ብረት ለበስ የጦር ተሸከርካሪዎችን ተጠቅሞ ነበር” ያሉት ፑቲን፤ “ሁኖም ግን እቅዳቸው አልተሳካላቸውም” ሲሉ ተናግረዋል።
“እንደአለመታደል ሆኖ በጥቃቱ የዜጎቻን ህይወት አልፏል” ያሉት ፑቲን፤ “ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻው አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል” ሲሉም ተነግረዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን “በምርጫ ቀን በሩሲያ ላይ የተቃጣው ጥቃት የኪቭ አስተዳደር ተከታታይ እና በጦር መሳሪያ የታገዙ ወንጀሎችን እየሰራ መሆንን ማሳያ ነው” ብለዋል።
ፑቲን አክለውም “እንዲህ አይነት የጠላት ጥቃቶች ያለ ቅጣት ሊታለፉ አይገባም” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ያገኙበት የሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርዓት ባሳለፍነው አርብ የጀመረ ሲሆን እስከ ዛሬ ቀጥሎ ይካሄዳል።
ምርጫው በመላው ሩሲያ እንዲሁም ሩሲያ በቅርቡ ከዩክሬን ወደ ራሷ በቀላቀለቻቸው ክልሎቸም ጭምር እየተካሄደ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ከቭላድሚር ፑቲን በተጨማሪ የክሬምሊንን ቁልፍ ሰልጣን ለመቆጣጠር ተስፋ ያደረጉ ሶስት እጩዎች "የማይቻለውን ውድድር" ተቀላቅለዋል።
የሩሲያ ማዕከላዊ ምርጫ ኮሚሽን ከፑቲን ጋር የሚፎካከሩ ሶስት እጩዎችን መመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን፤ እጩዎቹም ቭላዲስላቭ ዳቫንኮቭ፣ ሊዮኒድ ስሉትስኪ እና ኒኮላይ ካሪቶኖቭን ናቸው ተብሏል።
በምርጫው ለፑቲን ከፍተኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ተጠብቀው የነበሩት ዋነኛው ተቃዋሚ በእጩነት ሳይቀርቡ ቀርተዋል ነው የተባለው።
የሩሲያ ማዕከላዊ ምርጫ ኮሚሽን ዋነኛውን የተቃዋሚ ተፎካካሪ ቦሪስ ናድዘሀዲን ከፉክክሩ ውጪ ያደረገው ፊርማ በማሰባሰብ ሂደት ለይ የማጭበርበር ተግባር ተገኝቶባቸዋል በሚል ነው።