በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ከቭላድሚር ፑቲን ጋር የሚፎካከሩ ሶስት እጩዎች ይፋ ተደርገዋል
የሩሲያ ማእከላዊ የምርጫ ኮሚሽን በ2024 የሩሰያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ከቭላድሚር ፑቲን ጋር የሚፎካከሩ ሶስት እጩዎች መመዝገቡን አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ያገኙበት የሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከፊታችን አርብ መጋቢት 6 እስከ እሁድ መጋት 8 ይካሄዳል።
ፑቲን ምርጫውን በትልቅ ልዩነት እንደሚያሸንፉ ግምት ቢሰጣቸውም፤ የክሬምሊንን ቁልፍ ሰልጣን ለመቆጣጠር ተስፋ ያደረጉ ሶስት እጩዎች "የማይቻለውን ውድድር" ተቀላቅለዋል ነው የተባለው።
የሩሲያ ማዕከላዊ ምርጫ ኮሚሽን ከፑቲን ጋር የሚፎካከሩ ሶስት እጩዎችን መመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን፤ እጩዎቹም ቭላዲስላቭ ዳቫንኮቭ፣ ሊዮኒድ ስሉትስኪ እና ኒኮላይ ካሪቶኖቭን ናቸው ተብሏል።
“ዳግም የተመለሰው" ካሪቶኖቭ
በፓርላማ ውስጥ በተወከሉት የክሬምሊን ወዳጅ ፓርቲዎች ውስጥ ከተመረጡት ሰዎች መካከል የኮሚኒስት ፓርቲው ኒኮላይ ካሪቶኖቭ ይገኝበታል።
ኮሚኒስት ፓርቲው ሩሲያ በምታካሂዳቸው በእያንዳንዱ ምርጫ እጩ እንዲያቀርብ የተፈቀደለት ፓርቲ ቢሆንም ከፑቲን ከተሳተፉበት የመጀመርያው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኋላ አንድ አምስተኛውን ያህል ድምጽ አግኝቶ አያውቅም።
የ75 ዓመቱ እጩ ኒኮላይ ካሪቶኖቭ በ2004 በተካሄደው ፕሬዝዳናታዊ ምርጫ ላይ ከፑቲን ጋር ተፎካክረው 2ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቀቻውም ይታወሳል።
“ኤክስፐርቱ” ስሉትስኪ
የሩሲያ ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ የሆኑት ሊዮኒድ ስሉትስኪ ከፕሬዝዳት ፑቲን ጋር የማይቻለውን ፍክክር ለማድረግ በዕጩነት ከቀረቡት ውስጥ ናቸው።
የ56 ዓመቱ ሊዮኒድ ስሉትስኪ የፓርቲያቸው መሪ እንዲሁም በሩሲያ ዱማ (ፓርላማ) ውስጥ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ኮሚቴ ሰብሰቢ ናቸው። በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ስሉትስኪ የሩሲያ የሰላም ፋውንዴሽን የቦርድ ሊቀመንበር ናቸው።
ስሉትስኪ ሩሲያን በመወከል በአውሮፓ፣ ፈረንሣይ እና ቼችኒያ በተለያዩ ተልእኮዎች ውስጥ የሩሲያ ልኡክ አባል በመሆንም ማገልጋለቸው ነው የተነገረው።
“ምክትሉ”ዳቫንኮቭ
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሶስተኛ የቭላድሚር ፑቲን ተፎካካሪ የሆነው የቀረቡት ቭላዲስላቭ ዳቫንኮቭ ሲሆኑ፤ በሩሲያ ዱማ (የታችኛው ምክር ቤት) ምክትል አፈ ጉባዔ እና የኒው ፒፕል ፓርቲ አባል ናቸው።
በፈረንጆቹ 1984 በስሞልንስክ ከተማ የተወለዱት ቭላዲስላቭ ዳቫንኮቭ የዩክሬኖቹ ዶኔስክ እና ሉሃስክ ክልሎች ወደ ሩሲያ እንዲቀላቀሉ የሩሲያ ዱማ (ፓርላማ) ውሳኔ እንዲያሰለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው ተብሏል።
ሶስቱም እጩዎች ክሬምሊን እና ፖሊሲዎቹን እንዲሁም በፈረንጆቹ በየካቲት ወር 2022 የጀመረውን የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የሚደግፉ መሆናቸው ተነግሯል።
በምርጫው ለፑቲን ከፍተኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ተጠብቀው የነበሩት ዋነኛው ተቃዋሚ በእጩነት ሳይቀርቡ ቀርተዋል ነው የተባለው።
የሩሲያ ማዕከላዊ ምርጫ ኮሚሽን ዋነኛውን የተቃዋሚ ተፎካካሪ ቦሪስ ናድዘሀዲን ከፉክክሩ ውጪ ያደረገው ፊርማ በማሰባሰብ ሂደት ለይ የማጭበርበር ተግባር ተገኝቶባቸዋል በሚል ነው።
ከሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ውጪ የተደረጉት ቦሪስ ናድዘሀዲን ሩሰያ በዩክሬን ውስጥ እያደረገች ያለውን ጦርነት ትልቅ ስህተት በሚል ይቃወሙታል።
የ71 ዓመቱ ቭላድሚር ፑቲን በዘንድሮው ምርጫ ላይ ገዢው ፓርቲ ዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲን ወክለው ሳይሆን በግላቸው ነው የሚወዳደሩት ተብሏል።