ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ከቀድሞ ሶቬት ሀገራት ውጭ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉዞ ኢራንን ጎበኙ
ፑቲን ከቱርኩ ፕሬዝደንት ኦርዶጋን ጋርም በኢራን ይመክሯሉ
ከኢራን ጋር "በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች አቋማችን ተቀራራቢ ወይም ተመሳሳይ ነው" ብለዋል የፑቲን የውጭ ፖሊሲ አማካሪ
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ከቀድሞ የሶቬት ሀገራት ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢራንን በመጎብኘት የኢራኑን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒን አግኝተዋል፡፡
ፑቲን ፊታቸውን ወደ ህንድ፣ ኢራን እና ቻይና በማዞር የምእራባውያን ሀገራት ሩሲያን በኢኮኖሚ የማሽመድመድ እቅድ ላይ ጥላ ማጥላቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ሩሲያ በዩክሬን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” መጀመሯን ተከትሎ ይህን የሚቃወሙት ምእራባውያን ሀገራት በታሪክ ከባድ ነው የተባለውን ማእቀብ በሩሲያ ላይ ጥለዋል፤ እየጣሉም ነው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸው በሳኡዲ አረቢያ ካጠናቀቁ ሶስት ቀን በኋላ የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ከኢራኑ ጠቅላይ መሪ እና በፈረንጆቹ በ1989 ወደ ስልጣን ከመጡት አሊ ካሚኒ ጋር ለመወያየት ኢራን ደርሰዋል፡፡
"ከካሜኔ ጋር ያለው ግንኙነት በጣም አስፈላጊ ነው" ሲሉ የፑቲን የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ በሞስኮ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ "በሁለትዮሽ እና በአለምአቀፍ አጀንዳዎች ላይ በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እምነት የሚጣልበት ውይይት በመካከላቸው ተፈጥሯል" ብለዋል አማካሪው፡፡
ከኢራን ጋር "በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች አቋማችን ተቀራራቢ ወይም ተመሳሳይ ነው።" ብለዋል የፑቲን የውጭ ፖሊሲ አማካሪ
የፑቲን የኢራን ጉብኝት ከቱርክ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር የሚገጣጠም ሲሆን ሁለቱ መሪዎች ቴህራን ላይ በመገናኘት የዩክሬን የጥቁር ባህር እህል ወደ ውጭ መላክን ለማስቀጠል ያለመ ስምምነት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቱርክ በሰሜን ሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻ የመክፈት እቅድ አላት፤ ነገርግን ሩሲያ ይህን ትቃወማለች፡፡ ሁለቱ መሪዎች በዚህ ጉዳይም ይመክራሉ ተብሏል፡፡
ሩሲያ እና ኢራን ምእራባውያን ሀገራት የሶሪያ የእርስበእርስ ጦርነት ከተጀመረ ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ ከስልጣን እንዲወገድ የሚፈልጉት የሶሪያ መሪ በሽር አላሳድን ይደግፋሉ፡፡