ሩሲያ በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዲያበቃ እንደምትፈልግ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ
ፑቱን፤ ሁሉም የትጥቅ ግጭቶች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መቋጨታቸው አይቀሬ ነውም ብለዋል
ሩሲያ ለድርድር ዝግጁ መሆኗን ደጋግማ ብትገልጽም ዩክሬንና አጋሮቿ ግን“ግዜ ለመግዛት የምትጠቀምበት ዘዴ ነው” ይላሉ
ሩሲያ በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዲያበቃ እንደምትፈልግ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ፡፡
ፑቲን ይህን ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የዩክሬኑን አቻቸው ቮሎዲሚር ዘሌንስኪን በዋይት ሀውስ ተቀብለው ባነጋገሩበትና ዋሽንግተን በጦርነት ውስጥ ላለችው ኪቭ የምታደርገው ድጋፍ ቀጣይ እና የማይናወጥ መሆኑ ቃል በገቡበት ማግስት መሆኑ ነው።
"ግባችን የወታደራዊ ግጭትን መንኮራኩር ማሽከርከር አይደለም ፣ ግን በተቃራኒው ይህንን ጦርነት ማቆም ነው" ብለዋል ፑቲን።
ጦርነቱ ይቁም ከተባለ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ማካተቱ አይቀሬ ነው ያሉት ፑቲን፤ ይህን እውን ለማድረግ የተቻለንን ጥረት ሁሉ እናደረጋለም ብለዋል፡፡
ሩሲያ ለድርድር ዝግጁ መሆኗን ደጋግማ ብትገልጽም ዩክሬን እና አጋሮቿ ግን ሞስኮ በመልሶ ማጥቃት የደረሰባትን ተከታታይ ሽንፈት ተክተሎ ካፈገፈገች በኋላ ጊዜ ለመግዛት የምትጠቀመው ዘዴ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይነገራል፡፡
የሩሲያ የጦርነት ማቆም ፍላጎት ከልብ እንደሆነ የሚናገሩት ፑቲን ግን አሁንም “ጦርነት ይብቃ!” በማለት ላይ መሆናቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
"ብዙ ጊዜ ተናግሬአለሁ፤ ጠላትነትን ማባባስ ፍትሃዊ ያልሆነ ኪሳራ ያስከትላል”ም ነው ያሉት ፑቲን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡
ሁሉም የትጥቅ ግጭቶች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መቋጨታቸው አይቀሬ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
“ ይዋል ይደር እንጂ ማንኛውም ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ተቀምጠው ስምምነት ያደርጋሉ፤ ይህ እውነታ አሁን እየተቃወሙት ባሉ ሰዎች በኩል ሲመጣ የተሻለ ይሆናል፤ በዚህ ተስፋ ቆርጠን አናውቅም”ም ብለዋል ፑቲን፡፡
ነገር ግን ነገሮች ገፍተው ከመጡ ሞስኮ ከኪቭም ሆነ አጋሮቿ ሊቃጣባት የሚችልን አደጋ ለመመከት አቅሙ እንዳለት አስጠንቅቀዋል፡፡
ሩሲያ፤ ጆ-ባይደን ለዩክሬን ፕሬዝዳንት ለማስጠት ቃል የገቡትን የፓትሪዮት አየር መከላከያ ስርዓትን ለመከላከል የሚያስችል መንገድ እንደምታገኝም ጭምር ገልጸዋል ፕሬዝዳንት ፑቲን፡፡
እሱ (መሳሪያው) “በጣም ያረጀ ነው” እንደ ሩሲያ ኤስ-300 የመከላከያ ስርዓት አይሰራም ያሉት ፑቲን፤ ሩሲያን የፓትሪዮት አየር መከላከያ ስርዓትን ለማክሸፍ "የምንጊዜም መድኃኒት ታገኛለች" ሲሉም ዝተዋል፡፡
“ኪቭና አጋሮቿ ይህን የሚያደርጉት በከንቱ ነው፤ ትርፉ ግጭቱን ማራዘም ብቻ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
በሞስኮ ላይ የሚጣል ማዕቀብም ሆነ ለዩክሬን የሚደረግ ማንኛውም ድጋፍ በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው የጎላ ተጽእኖ እንደማይኖርም ጭምር ተናግረዋል፡፡
ሞስኮ ፤ ኪቭ ለንግግር በሯን ዝግ አድርጋለች ብላ ብትከስም፤ ዩክሬን በበኩሏ ከመነጋገራችን በፊት ሩሲያ ጥቃቷን በማቆም የያዛችውን ግዛት ለቃ ትውጣ እያለች ነው፡፡