የዓለምን የኃይል ሚዛን ይለውጣል ስለሚባለው የሩሲያ "ሳርማት" ሚሳኤል ምን ያውቃሉ?
"ሳርማት" ሚሳኤል በሰዓት 25 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ፍጥነት አለው
"ሳርማት" ባሊስቲክ ሚሳኤል ሩሲያን ለሚቀጥሉት 50 አመታት ሊከላከል የሚችል ነው ተብሏል
በጦርነት ላይ የምትገኘው ሩሲያ ጥቅም ላይ እንደምታውለው የሚጠበቀው "ሳርማት" ባሊስቲክ ሚሳኤል የዓለማችን የኃይል ሚዛን ይለውጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይነገራል፡፡
አስፈሪው የሩስያ "ሳርማት" ባሊስቲክ ሚሳኤል የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) "ሰይጣን 2" ብሎ የሚጠራው ሲሆን በቅርቡ ጥቅም ላይ እንደሚውል የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናግረዋል፡፡
ፑቲን የ"ሚሳኤሎችን ንጉስ" ብለው የሚጠሩት ሚሳኤል የመጠቀም እቅድ እንዳላቸው ያስታወቁት በጦር ኃይሉ ውስጥ ካሉ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች ጋር ዛሬ ባደረጉት ዘለግ ያለ ስብሰባ ላይ ነው፡፡
የፑቲን የዛሬ ዜና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ባህር ማዶ ተሳግረው የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ለማድረግ ወደ ዋሽንግተን ባቀኑበት ቀን መሆኑ ነው፡፡
ፑቲን ሳርማትን መቼ ወደ አገልግሎት እንደሚገባ በግልጽ ያሉት ነገር ባይኖርም ከዚህ ቀደም በዚህ ዓመት መጨረሻ ሊሆን እንደሚችል አይዘነጋም፡፡፡
"ሳርማት" ምንድን ነው?
“ሳርማት ከሶስት እና ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ፑቲን "ገደብ የለሽ" በማለት ሲጠሩት የነበረ ሚሳኤል ነው፡፡
በተጨማሪም ፑቲን በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ የሚሳኤሉን ሙከራ በተካሄደበት ወቅት " ይህ መሳሪያ (ሳርማት) ሩሲያን ለማስፈራራት የሚሞክሩትን ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው" ሲሉ የገለጹት አስፈሪ ሚሳኤል ነው፡፡
ሚሳኤሉ ከ500 ቶን በላይ ክብደት ያለው የዘመኑ መሳሪያ ተደርጎ የሚቆጠር እንዲሁም የተሰራው ከአስር አመታት በፊት ሲሆን የሩሲያ የኒውክሌር መከላከያ ዋና አካል ነው።
ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ4ኛው እስከ 5ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የሳርማትያ ህዝብ ስም የተሰየመው ሚሳኤሉ፤ በምዕራቡ ዓለም "ሰይጣን 2" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከዘመናዊው የጸረ-አውሮፕላን ስርዓቶች ሁሉ የላቀ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡
ባለሶስት ሜትር ዲያሜትሩ ሚሳኤል 18ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በሰዓት በ25 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ፍጥነት መምዘግዘግ የሚችል ነው፡፡
አርኤስ-28 ሳርማት ሚሳኤል ቴክሳስን የሚያክል አካባቢ ጠራርጎ ለማጥፋት የሚያስችል ትልቅ የኒውክሌር ጭነት መሸከም ይችላልም ተብሏል።
በ2018 በፑቲን ከተገለጹት ስድስት ስልታዊ የሩሲያ የጦር መሳሪያዎች አንዱ ነው
የሩሲያ "ማኬቭ" ሚሳኤል ኢንዱስትሪ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ቭላድሚር ደግትያር "ሳርማት" በመባል የሚታወቀው ስትራቴጂካዊ አህጉር አቀፍ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች የሩስያን ደህንነት ለበርካታ አስርት ዓመታት ዋስትና የሚሰጥ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
በነዳጅም ጭምር እንደሚሰራ የሚነገርለት አስፈሪው ሳርማት ሚሳኤል ሩሲያን ለሚቀጥሉት 50 አመታት ሊከላከል የሚችል መሆኑም ነው የተናገሩት ደግትያር ከ"ሮሲይስካ ጋዜጣ"ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡