ፑቲን የሩሲያን የኒዩክሌር አጠቃቀም ህግ በማጽደቅ አሜሪካን አስጠነቀቁ
ዩክሬን ከአሜሪካ የተላከላትን ሚሳኤል ወደ ሩሲያ ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ መተኮሷን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል
በአለም ላይ ከተመረቱ የኒዩክሌር አረሮች 88 በመቶው በሩሲያና አሜሪካ ይገኛሉ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአሜሪካ አዲስ የማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ የተሻሻለውንና የሩሲያን የኒዩክሌር መሳሪያ አጠቃቀም የሚወስነው ህግ ማጽደቃቸውን ክሬምሊን አስታውቋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዩክሬን ከአሜሪካ በተላኩላት ሚሳኤሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩሲያ ግዛት ጥቃት መፈጸሟን በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኬቭ ለወራት ስትጠይቀው የነበረውን ከምዕራባውያን የተላኩላትን ሚሳኤሎች ወደ ሩሲያ ዘልቃ ጥቃት ለማድረስ ይፈቀድልኝ ጥያቄ በትናንትናው እለት አጽድቀዋል።
ውሳኔው "አሜሪካ እና የኔቶ አባል ሀገራት በሩሲያ ላይ ጦርነት እንደከፈቱ ያሳያል" ያለው ክሬምሊን ፕሬዝዳንት ፑቲን ዋሽንግተን የኒዩክሌር ጦርነት ከሚያስነሳ ተግባሯ እንድትታቀብ ማሳሰባቸውን ጠቁሟል።
በብርያንስክ ክልል የሚገኝ የሩሲያን ወታደራዊ ጣቢያ መቷል የተባለውና እስከ 300 ኪሎሜትሮች የሚጓዘው የአሜሪካ ሚሳኤል (ATACMS) የዋሽንግተን እና ሞስኮን ፍጥጫ አባብሷል።
ሩሲያ በ2020 በይፋ ያወጣችውን የኒዩክሌር ህግ ማሻሻሏን ስትገልጽ የቆየች ሲሆን፥ ባይደን ለኬቭ ይሁንታ በሰጡ ማግስት ፑቲን ማሻሻያውን ማጽደቃቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ማሻሻያው ኒዩክሌር ያልታጠቁ ሀገራት ከታጠቁት ጋር በመተባበር በሩሲያ ላይ ጥቃት ካደረሱ በሞስኮ ላይ “የጋራ ጥቃት” እንደከፈቱ ይቆጠራል የሚል ሃሳብ አካቷል።
ሩሲያ የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን መቼ መጠቀም እንዳለባት በግልጽ የሰፈረበት ህግ፥ ድንበር አቋራጭ የሚሳኤል፣ የአየር እና ድሮን ጥቃት ከተፈጸመባት አውዳሚዎቹን መሳሪያዎች መጠቀም እንደምትጀምር የሚፈቅድ ነው።
ሞስኮ አጋሯ ቤላሩስ ከተወረረች እና በኮንቬንሽናል መሳሪያዎች ጥቃት ከደረሰባት የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን ልትጠቀም እንደምትችልም ነው የጸደቀው የኒዩክሌር አጠቃቀም ህግ የሚያሳየው።
በአለም ላይ ከተመረቱ የኒዩክሌር አረሮች 88 በመቶው በሩሲያ እና አሜሪካ ነው የሚገኘው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዚህ ቀደም “ኒዩክሌር የዜጎቻችን ደህንነት ለማስጠበቅም ሆነ የአለም ስርአት ሚዛንን ለማስተካከል ዋነኛው አማራጭ ነው፤ ምዕራባውያን በእሳት ከመጫወት ሊቆጠቡ ይገባል” ሲሉ ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው።
በዛሬው እለት 1ሺኛ ቀኑን የያዘው የዩክሬን ጦርነት ሩሲያ እና ምዕራባውያን ከ1962ቱ የኩባ ሚሳኤል ቀውስ በኋላ ከባድ ፍጥጫ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል።