ሞስኮ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ከምዕራባውያን ጋር የገባችበት ፍጥጫ ሶስተኛውን የአለም ጦርነት እንዳይቀሰቅስ ስጋት ፈጥሯል
ሩሲያ በዛሬው እለት ከ79 አመት በፊት ሶቪየት ህብረት የናዚ ጀርመን ወራሪ ሃይልን ያሸነፈችበትን የድል በዓል እያከበረች ነው።
ሶቪየት ህብረት ከፈራረሰች ከስምንት አመት በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቀዩ አደባባይ በሚካሄደው በዓል ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።
ሞስኮ ከዩክሬኑ ጦርነት በኋላ አነስ ያለም ቢሆን ወታደራዊ ትርኢት እንደምታሳይ ነው የተነገረው።
በሁለተኛው የአለም ጦርነት የናዚ ጀርመን እና የፋሽስት ጣሊያን ሃይልን ለማሸነፍ ከተባበሯት ሀገራት ጋር ግንኙነቷ ይበልጥ በሻከረበት ወቅት የሚከበረው የድል በዓል ለሩሲያውያን ትልቅ ስፍራ አለው።
“አባት ሀገራቸውን ለመጠበቅ መስዋዕትነት ለከፈሉት ሁሉ ትልቅ ክብር አለኝ” ለሚሉት ለፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የበዓሉ ትርጉም ከፍ ያለ ነው።
አባታቸው በሁለተኛው የአለም ጦርነት የናዚ ጀርመን ሃይልን መዋጋታቸውንና ጦርነቱ ያስከተለውን ጠባሳ ደጋግመው የሚያነሱት ፑቲን፥ ምዕራባውያን ሶቪየት ህብረት የሂትለርን ጦር በማሸነፉ ረገድ የነበራትን ድርሻ ዘንግተዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።
የ71 አመቱ ፕሬዝዳንት ከትናንት በስቲያ ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን ቃለመሃላ ሲፈጽሙም የዩክሬኑ ጦርነት የሁለተኛው የአለም ጦርነት የሶቪየት ህብረትን ብርታት ካለመረዳት የመነጨ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ መራሹ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋትንም ከናዚ ጀርመን ፍላጎት ጋር እንደሚያመሳስሉት አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ዩክሬንና ምዕራባውያን አጋሮቿ ግን ሉአላዊ ሀገር በመውረር መሬት የመያዝ “ያረጀ የንጉሳዊ አገዛዝ” እየተከተሉ ያሉት ፑቲን ናቸው በማለት ይወቅሳሉ።
የዩክሬንን ከ18 በመቶ በላይ ግዛት በቁጥጥሯ ስር ያስገባችው ሞስኮ በበኩሏ ጦርነቱ ከኬቭ ጋር ሳይሆን አይዞሽ ከሚሏት “የናዚ አስተሳሰብ አራማጅ” ምዕራባውያን ሀገራት ጋር እንደሆነ ትገልጻለች።
በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸው የዩክሬን መሬቶችም ከአመታት በፊት የታላቋ ሩሲያ አካል እንደነበሩና በመጥቀስ ወቀሳውን ውድቅ ታደርጋለች።
ዛሬ እያከበረችው ያለውን የድል በዓልም ብርታቷን ለአለም ለማሳየት ትጠቀምበታለች።
ሶቪየት ህብረት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ከ27 ሚሊየን በላይ ዜጎቿን ማጣቷ ይነገራል።
ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን “አክሲስ ፓወር” በሚል አለምን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ “ከተባበሩት ሃይሎች” አሜሪካ፣ ሶቪየት ህብረት፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ጋር ያደረጉት ጦርነት በርካታ ሀገራት የተሳተፉበትና ከወቅቱ የአለም ህዝብ 3 በመቶው ያለቀበት ነው።
በዩክሬን ምክንያት ሶስተኛው የአለም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋቱ ባየለበት በዚህ ወቅት ሩሲያ ታክቲካል የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች ሙከራ እንዲጀምር አዛለች።
በሁለተኛው የአለም ጦርነት አብረዋት የተሰለፉት ሀገራት አሁን ዋነኛ የደህንነት ስጋት እንደሆኑባት ገልጻለች።
አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ለዩክሬን ከጦር መሳሪያ እስከ ወታደር በመላክ ኬቭን ከሞስኮ ጋር ሃያቸውን የሚፈታተሹባት የጦር ሜዳ ካደረጓት ከሁለት አመት በላይ ተቆጥሯል።