ዩክሬን የህግ ታራሚዎችን ወደ ጦር ሜዳ ልትልክ ነው
የዩክሬን ፓርላማ ከባድ ወንጀል ከፈጸሙት ውጪ ታራሚዎች ለሀገሪቱ ጦር እንዲዋጉ የሚፈቅድ ህግ አጽድቋል
የዩክሬን ጦር በታህሳስ ወር ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮች እንዲቀርብለት መጠየቁ ይታወሳል
ከሩሲያ ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት የወታደሮች ቁጥር መመናመን ያሳሰባት ዩክሬን የህግ ታራሚዎችን ወደ ጦር ሜዳ ልትልክ ነው ተባለ።
የሀገሪቱ ፓርላማ በዛሬው እለት ከባድ ወንጀል ከፈጸሙት ውጪ ታራሚዎች ጦሩን በፈቃዳቸውን ተቀላቅለው ለሀገራቸው እንዲዋጉ የሚፈቅድ ህግ አጽድቋል።
የፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ፓርቲ ሃላፊ ኦሌና ሹልያክ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ ፓርላማው በጎፈቃደኛ ታራሚዎችን ወደ ጦር ግንባር ለመላክ የቀረበውን ረቂቅ ህግ አጽድቋል ብለዋል።
የጸደቀው ህግ የፓርላማው አፈጉባኤና ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ከፈረሙበት በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል መባሉንም ኬቭ ኢንዲፐንደንት አስነብቧል።
የዩክሬን ፍትህ ሚኒስቴር 50 ሺህ የተፈረደባቸውና ከ26 ሺህ በላይ ቅጣት ያልተላለፈባቸውና በቅርብ ጊዜ የታሰሩ ዩክሬናውያን የሀገሪቱን ጦር ተቀላቅለው ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት ፍላጎታቸውን አሳውቀዋል ብሏል።
የተተኳሽ ጥይት እና ተዋጊ ወታደሮች እጥረት የመልሶ ማጥቃቱ እንዲጓተት ያደረገበት የዩክሬን ጦር ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮች እንደሚያስፈልጉት በታህሳስ ወር 2023 ማሳወቁ ይታወሳል።
ታራሚዎችን ወደ ጦር ግንባር መላክ የሚፈቅደው ረቂቅ ህግም ባለፈው መጋቢት ወር መቅረቡን የሚያወሳው የሩሲያው ታስ የዜና ወኪል፥ ዛሬ በጸደቀው ህግ በከባድ ወንጀል የተፈረደባቸው ታራሚዎች የዩክሬንን ጦር እንዲቀላቀሉ እንደማይፈቀድላቸው መስፈሩን ዘግቧል።
የዩክሬንን ብሄራዊ ደህንነት የጣሉ፣ በግድያ ወንጀል፣ በአስገድዶ መድፈርና ሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው የተፈረደባቸው ታራሚዎች የዩክሬንን ጦር አይቀላቀሉም ተብሏል።
አደንዛዥ እጽ ወይም አልኮል ወስደው ሲያሽከርክሩ የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ የመኪና አደጋ ያደረሱ ፍርደኞችም ጦሩን ከማይቀላቀሉት ውስጥ ናቸው።
ከተጠቀሱት ወንጀሎች ውጭ በቀላል ወንጀል ተከሰው ቅጣታቸውን በማረሚያ ቤት እያሳለፉ የሚገኙ ታራሚዎች ፈቃደኝነታቸው ተጠይቆና የጤናቸው ሁኔታ ተመርምሮ ምልምል ወታደር ይሆናሉ ተብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ በምስራቃዊ ዩክሬን በዶኔስክና ካርኬቭ ግዛቶች ሁለት ከተሞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ዩክሬን ካለፈው አመት ሰኔ ወር ጀምሮ በሞስኮ የተያዙብኝን ግዛቶች ለማስመለስ የመልሶ ማጥቃት እጀምራለሁ ብትልም የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ መዘግየትን በመጥቀስ መከላከል ላይ ብቻ አተኩራለች።