ፑቲን ምርጫውን ማሸነፋቸው ሩሲያን ለረጅም ዓመት የመምራት ታሪክን ከስታሊን እንዲረከቡ ያሰችላቸዋል
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ተገለጸ።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ያገኙበት የሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርዓት ባሳለፍነው አርብ የጀመረ ሲሆን እስከ ትናት ቀጥሎ ተካሂዷል።
የድምጽ አሰጣጡ ትናንት መጠናቀቁን ተከትሎ ቆጠራ እየተካሄደ ሲሆን፤ እስካሁን በተደረገው ቆጠራ ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት እየመሩ መሆኑ ተነግሯል።
የሩሲያ ማእከላዊ የምርጫ ኮሚሽን ሰብሳቢ እንዳስታወቁት፤ እስካሁን በተደረገ የድምጽ ቆጠራ ቭላድሚር ፑቲን 88 በመቶ ደምጽ በመግኘት በሰፊ ልዩነት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል።
በዚህም ፑቲንእስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ማለትም ለቀጣይ 6 ዓመታት በስልጣን ላይ የሚቆዩበትን እድል በድጋሚ አግኝተዋል ነው የተባለው።
ፑቲን በዘንድሮው ምርጫ ማሸነፋቸው ከ200 ዓመታ በኋላ ሩሲያን ለረጅም ዓመታት በመምራት የሚታወቁትን የጆሴፍ ስታሊንን ክብረ ወሰን በእጃቸው እንዲያስገቡ ያስችላቸዋል።
ፑቲን ውጤቱን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ሩሲያውን ለሰጧቸው ድጋፍ እና እምነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“ይህ አንድነት በኢኮኖሚ ፣ በሰብአዊ ልማት ፣ በማህበራዊ ልማት ፕሮጀክቶች ግቦች ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንሠራ ያስችለናል” ብለዋል።
ሩሲያ ያካሄደችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከየትኛውም የምእራባውያን ሀገራት የተሸለ እና በጣም ግልጸኝነት የታየበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ከቭላድሚር ፑቲን በተጨማሪ የክሬምሊንን ቁልፍ ሰልጣን ለመቆጣጠር ተስፋ ያደረጉ ሶስት እጩዎች "የማይቻለውን ውድድር" ተቀላቅለው ነበር።
ከፑቲን ጋር ለመፎካር በእጩነት ቀርበው የነበሩ እጩዎቹም ቭላዲስላቭ ዳቫንኮቭ፣ ሊዮኒድ ስሉትስኪ እና ኒኮላይ ካሪቶኖቭን ሲሆኑ፤ እያንዳንዳቸው ከ4 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘት አልቻሉም ተብሏል።
በምርጫው ለፑቲን ከፍተኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ተጠብቀው የነበሩት ዋነኛው ተቃዋሚ ቦሪስ ናድዘሀዲን ከውድድሩ ውጪ መደረጋቸውም ይታወሳል።