የአሜሪካ ባለስልጣናት በጦርነቱ 70 ሺህ ዩክሬን ወታሮችና 120 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ሞተዋል ብለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ባለፉት 2 ዓመታት ውስጥ 31 ሺህ ወታደሮቿ እንደሞቱባት ተናግረዋል።
ዘለንስኪ በትናንትናው እለት ባደረጉት ንግግር ከዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩክሬን ወታደሮችን የሞት መጠን ይፋ አደርገዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በኪቭ በሰጡት መግለጫ፤ በጦርነቱ የቆሰሉ ወታደሮቻውን ቁጥር ግልጽ አላደረጉም የተባለ ሲሆን፤ መረጃውን ይፋ ማደረግ ለሩሲያ እቅድ ሊጠቅም ይችላል በሚል መደበቃቸው ተነግሯል።
“እንደሚወራው 300 ሺህ አሊም 150 ሺህ ሳይሆን፤ 31 ሺህ ወታደሮቻችንን አጥተናል” ያሉት ዘለንስኪ፤ “የሩሲያው ፕሬዘዳት ፑቲን እየዋሹ ነው” ብለዋል።
ሆኖም ግን “31 ሺህ ወታደሮቻችንን ማጣት ለእኛ ትልቅ ኪሳራ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ።
ዩክሬን ከፈረንጆቹ 2022 መጨረሻ ወዲህ የሞቱባት ወታደሮቿን ቁጥር ግልጽ አድርጋ የማታውቅ ሲሆን፤ በወቅቱም ዩክሬን ባወጣችው መረጃ የሞቱ ወታደሮቿ ቁጥር 13 ሺህ ነው ብላ ነበር።
የአሜሪካው ኒው ዮርክ ታይምስ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ ባወጣው መረጃ በጦርነቱ 70 ሺህ ዩክሬን ወታሮችና 120 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ሞተዋል ብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው በጦርነቱ የሞቱ የሩሲያ ወታደሮች ቁጥር 180 ሺህ እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር የገጠመችውን ጦርነት 2ኛ ዓመት አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር “ዩክሬን ሩሲያን ታሸንፋለች” ብለዋል።
“ማናችንም ብንሆን ዩክሬን እንዲያበቃላት አንፈቅድም” ብለዋል ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ባደረጉት ንግግር።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ባሳለፍነው ቅዳሜ ሁለትኛ ዓመቱን ደፍኗል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ማካሄድ መጀመራቸውን ያወጁት በፈረንጆቹ የካቲት 24 2022 ነበር።
ዘመቻው እንደተባለው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ግን አልሆነም፤ በሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈትና ለጉዳት ዳርጎ ሶስተኛ ዓመቱን አሃዱ ብሏል።