ፑቲን እና ሺ አሜሪካን የሚቃወም "አዲስ ዘመን"የተሰኘ የጋራ መግለጫ ፈረሙ
ሺ ሁለቱ ሀገራት አለም በክፍለዘመኑ አይቶት የማያውቀውን ለውጥ የማምጣት እድል እንዳለቸው ለፑቲን ነግረዋቸዋል
ምዕራባውያን ቻይና በዩክሬን ጦርነት የከፈተችውን ሩሲያን በግልጽ እንድታወግዝ ጫና ቢያሳድሩም፣ ቻይና አልተቀበለቻቸውም
የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ እና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን፣ የአሜሪካ ዋነኛ ተቀናቃኝ በሆኑት ሁለት ኃያላን ሀገራት መካከል አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ለመክፈት ቃል መግባታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝደንት ሺ ፕሬዝደንት ፑቲንን ቤጂንግ በሚገኘው 'ግሬት ሆል ኦፍ ዘ ፒፕል' ፊት ለፊት የተቀበሏቸው ሲሆን፣ ለክብራቸው በቲያናንሜን አደባባይ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶላቸዋል።
ፑቲን በፈረንጆቹ 2022 በዩክሬን ላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ከመላካቸው ከቀናት በፊት ቤጂንግን በጎበኙበት ወቅት ቻይና እና ሩሲያ "ገደብ የለሽ" ግንኙነት ለማድረግ መወሰናቸውን ተናግረው ነበር።
ፑቲን እና ሺ በትናንትናው እለት ከታይዋን እና ዩክሬን እስከ ሰሜን ኮሪያ እና ሰላማዊ የኑክሌር ትብብር ድረስ ባሉ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን አሜሪካን የሚቃወም "አዲስ ምዕራፍ" የሚል የጋራ መግለጫም ተፈራርመዋል።
"አሁን ያለው የቻይና እና የሩሲያ ግንኙነት በጥረት የተገኘ ነው፤ ሁለቱም ወገኖች ከግንኙነቱ መጠቀም እና መንከባከብ አለባቸዉ" ሲሉ ፕሬዝደንት ሺ ለፑቲን ተናግረዋል።
"ቻይና የሁለቱን ሀገራት ልማት እውን እንዲሆን እና በዓለም ፍትሀዊነት እንዲኖር ለማድረግ በጋራ ለመስራት ፈቃደኛ ነች።"
በኔቶ እርዳታ የጦር መሳሪያ እርዳታ ከሚቀርብላት ጋር እየተዋጋች ያለችው ሩሲያ እና አሜሪካ እያደገ ባለው ወታራዊ አቅሟ እና በኢኮኖሚያዋ ላይ ጫና የምታደርግባት ቻይና በጋራ የሚቆሙበት ዲኦፖለቲካዊ ምክንያት አላቸው።
ሺ ሁለቱ ሀገራት አለም በክፍለዘመኑ አይቶት የማያውቀውን ለውጥ የማምጣት እድል እንዳለቸው ለፑቲን ነግረዋቸዋል።
ቻይና እና ሩሲያ በአሜሪካ የበላይነት የሚመራውን የዓለም ስርአት መቀየር ይፈልጋሉ። የሶቬት ህበረትን መውደቅ እና የቻይናን ለአስርት አመታት በቅኝ ግዛት ስር መቆየት እንደውርደት የማይቀበሉት ሁለቱ ሀገራት ምዕራባውያን እየተዳከሙ ናቸው የሚል ስእል ለመፍጠር እንደሚፈልጉ ተገልጿል።
ምዕራባውያን ቻይና በዩክሬን ጦርነት የከፈተችውን ሩሲያን በግልጽ እንድታወግዝ ጫና ቢያሳድሩም፣ ቻይና አልተቀበለቻቸውም።
ፕሬዝደንት ፑቲንም ቻይና ከጦርነቱ በፊት ያሉ ሁኔታዎችን ከግምት ስለምታስገባ ያቀረበችውን የዩክሬን የሰላም እቅደም እንደሚቀበሉት መናገራቸው ይያወሳል።
አሜሪካ ቻይናን እንደዋነኛ ተፎካካሪዋ ስታያት ሩሲያን ደግሞ አንደ ትልቅ የደህንነት ስጋት አድርጋ ትመለከታታለች።