ሩሲያ በካርኪቭ ግዛት የሚገኙ 5 የዩክሬን መንደሮችን መቆጣጠሯን አስታወቀች
የዩክሬን ባለስልጣናት ሩሲያ የዩክሬኗን ሁለተኛዋን ትልቅ ከተማ ካርኪቭን በከበበው የካርኪቭ ግዛት ጥቃት መክፈቷን ተናግረው ነበር
የካርኪቭ ጎረቤት የሆነችው የሩሲያዋ ቤልጎሮድ ግዛት በተደጋጋሚ የድሮን እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት ስታስተናግድ ቆይታለች
ሩሲያ በትናንትናው እለት ጥቃት በከፈተችበት በሰሜን ምስራቅ በምትገኘው የዩክሬኗ የካርኪቭ ግዛት አምስት መንደሮችን መቆጣጠሯን አስታወቀች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ የሩሲያ ኃይሎች ፕሌተንቪካ፣ኦሂርስቬ፣ ቦሪሲቪካ፣ ፕይልና እና ስትሪልችና የተባሉ አምስት መንደሮችን መቆጣጠር ችለዋል። ሁሉም መንደሮች ከሩሲያ ጋር ድንበርተኛ ናቸው ብሏል ሚኒስቴሩ።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው የሩሲያ ጦር ባለፈው የካቲት ወር አቭዲቪካን ከያዘ በኋላ በዝግታ እና ቀጣይነት ባለው መልክ ወደ ፊት እየገፋ ባለው የዶኔስክ ግዛት በደቡብ አቅጣጫ ኬራሚልክ የተባለችውን መንደር ይዟል።
የዩክሬን ባለስልጣናት በትናትናው እለት እለት ሩሲያ የዩክሬኗን ሁለተኛዋን ትልቅ ከተማ ካርኪቭን በከበበው የካርኪቭ ግዛት ጥቃት መክፈቷን ተናግረው ነበር።
የካርኪቭ ገዥ ኦሌህ ሲኒሁቦቭ እንደገለጹት የሩሲያ ኃይሎች አሁንም ጥቃታቸውን መቀጠላቸውን እና ወደፊት ለመግፋት እየሞከሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የሩሲያ ኃይሎች በየካቲት 2022 በካርኪቭ ላይ ጥቃት ከፍተው የነበረ ቢሆንም በዩክሬን ኃይሎች ፈጣን መልሶ ማጥቃት በዛው አመት መስከረም ወር ከአብዛኛው የግዛቷ ክፍል መውጣታቸው ይታፈሳል።
የካርኪቭ ጎረቤት የሆነችው የሩሲያዋ ቤልጎሮድ ግዛት በተደጋጋሚ የድሮን እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት ስታስተናግድ ቆይታለች።
ሩሲያ ካርኪቭን መጠቅለል ትፈልግ እንደሆነ ባለፈው መጋቢት የተጠየቁት የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን የሩሲያን ግዛት ከዩክሬን ከባድ መሳሪያ ኢላማ ውጭ ማድረግ የሚቻለው ከጦር ነጻ ቀጠና መመሰረት ሲቻል ብቻ ነው የሚል መልስ ነበር የሰጡት።
በምስራቅ እና በደቡብ ከ18 በመቶ በላይ የዩክሬንን ግዛት የያዘችው ሩሲያ፣ የ2023ቱ የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ከከሸፈ በኋላ ይዞታዋን እያስፋፋች ነው።