ኳታር የሀማስ ሃላፊዎችን ከዶሃ ለማስወጣት ተስማማች
ለረጅም አመታት የሀማስ መሪዎች መጠጊያ ሆና የዘለቀችው ዶሃ በአሜሪካ ግፊት መሪዎቹን እንደምታስወጣ ተሰምቷል
የሀማስ ጊዜያዊ መሪ ካሊድ ማሻልን ጨምሮ ሌሎች የቡድኑ የፖለቲካ ቢሮ አመራሮች በኳታር ይኖራሉ
ኳታር በሀገሪቱ የሚኖሩ ከፍተኛ የሀማስ አመራሮችን ለማስወጣት ከአሜሪካ የቀረበላትን ጥያቄ መቀበሏ ተሰማ፡፡
ሀማስ በ2012 በሶርያ የእርስ በእርስ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ዋና ቢሮውን ከደማስቆ ወደ ዶሃ አዘዋውሯል፡፡
የጥቅምት ሰባቱን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ “ኳታር በተለመደው መንገድ ከቡድኑ ጋር ግንኙነቷን መቀጠል እንደማትችል” ስታስጠነቅቅ ሰንብታለች፡፡
ሀገሪቱ በዶሃ የሚገኘውን የቡድኑን ዋና ቢሮ እንድትዘጋ እና ለሀላፊዎቹ ጥገኝነት ከመስጠት እንድትቆጠብ ጫና ስታደርግ መቆየቷን ሲኤንኤን የአሜሪካ እና ኳታር ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ዘገባው ሀማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ እና የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ የቀረበለትን ተደጋጋሚ ጥያቅ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፤ መሪዎቹ በማንኛውም የአሜሪካ አጋር ዋና ከተሞች ተቀባይነት ሊያገኙ አይገባም የሚል ሀሳብ በዋሽንግተን በኩል መንጸባረቁን ጠቅሷል፡፡
ሀማስ በነሀሴ ወር ሄርሽ ጎልድበርግ የተባለ ግለሰብን ጨምሮ አምስት የአሜሪካውን ዜግነት ያላቸውን ታጋቾችን ከገደለ በኋላ ከዋሽግተን የበረታው ግፊት ኳታር ሀላፊዎቹን ለማስወጣት የቀረበላትን ጥያቄ እንድትቀበል እንዳደረጋት ነው የተነገረው፡፡
አሜሪካ ከሁለት ሳምንት በፊት ኳታር መሪዎቹን እንድታስወጣ በጠየቀችው መሰረት ኳታር ከሳምንት በፊት ባለስልጣናቱ ከሀገሪቷ ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ሰጥታለች፡፡
በዚህም መሰረት የሀማስ ወቅታዊ መሪ ካሊድ ማሻልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በቅርቡ ዶሀን ለቀው እንዲወጡ ሊደረግ ይችላል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ ሀገሪቷን ለቀው ለመውጣት እስከ መቼ ጊዜ እንደተሰጣቸው እና ቀጣይ የሚያርፉበት ሀገር የት ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም፡፡
ነገር ግን ቱርክ ፣ ኢራን፣ ሊባኖስ እና አልጄርያ ቀጣዮቹ የሀማስ መሪዎች መጠጊያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ኳታር የሃማስ የባንክ ሂሳቦችን እንድታግድ እና የባለስልጣናቱን ንብረት እንድትይዝ ጠይቋል።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ሀማስ በአንድ ከፍተኛ ባለስልጣኑ በኩል በሰጠው ምላሽ “አመራሮቹን ከኳታር ማስወጣትን በተመለከተ እየተናፈሰ የሚገኘው መረጃ መሰረተ ቢስ እና በቡድኑ ላይ ጫና የመፍጠር ስልት ነው” ብሏል። ከዚህ ቀደምም የሃማስ መሪዎች ከዶሃ ሊወጡ ነው የሚሉ በትክክለኛ መረጃ ያልተደገፉ ዘገባዎች ሲወጡ መቆየታቸውን በማስታወስ።
ባለፈው አንድ አንድ አመት በእስራኤል እና ሀማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ዋና ተዋናይ ሆና የቆየችው ኳታር ከዚህ ውሳኔ በኋላ በድርድሩ የሚኖራት ሚና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
ዶሃ ከ2012 ጀምሮ የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ መቀመጫ ከመሆን ባሻገር ከ2018 ጀምሮ በእስራኤል እና አሜሪካ እውቅና ጋዛን ለሚያስተዳድረው ሀማስ ለሰራተኞች ደምዎዝ በሚል በየወሩ 15 ሚሊየን ዶላር ትሰጣለች፡፡