የፈረንሳዩ ኤር ፍራንስ እና የሆላንዱ ኬኤልኤም በጋራ 8 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ እንዳገኙ ተገልጿል
የኳታር አየር መንገድ በዓለም ዋንጫው ምክንያት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉ ተገለጸ።
ባሳለፍነው ሕዳር ወር ላይ በኳታር አስተናጋጅነት የተካሄደው የፊፋ 2022 ዓለም ዋንጫ ብዙ ክስተቶችን አሳይቶ አልፏል።
ኳታር ውድድሩን ለማዘጋጀት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ ያደረገች ቢሆንም አየር መንገዷ ከትርፉ ተቋዳሽ ሆኗል።
የኳታር አየር መንገድ የዓለም ዋንጫውን ለመመልከት ወደ ዶሀ ከመጡ ተጓዦች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ሲኤንኤን ዘግቧል።
የኳታር አየር መንገድ ከዓለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ ብቻ 140 ሺህ በረራዎችን በማድረግ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን አጓጉዟል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ውድድሩ ለኳታር አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችም ብዙ በረከቶችን አድርሷል።
የዓለም ዋንጫው ብቻ ሳይሆን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ጉዞ በመቀጠሉ እና ሰዎች ወደ ቀድሞ ህይወታቸው በመመለሳቸው የአየር መንገዶች ትርፍን እንዲያድግ አድርጓል ተብሏል።
የፈረንሳዩ ኤርፍራንስ እና የሆላንዱ ኬኤልኤም በጥምረት እየሰሩ ሲሆን ከፍተኛ ትርፍ ካተረፉ አየር መንገዶች መካከል ዋነኞቹ ሆነዋል።
ሁለቱ አየር መንገዶች በጥምረት ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ አትርፈዋል የተባለ ሲሆን ትርፉ ካለፈው ዓመት ወቅት ሲነጻጸር በአንድ ቢሊዮን ብልጫ አለው ተብሏል።
እነዚህ አየር መንገዶች ፈረንሳይ በሚቀጥለው ዓመት የኦሎምፒክ ውድድርን ማዘጋጀቷን ተከትሎ ትርፋቸው እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል።
ይሁንና በአየር መንገዶች ላይ የሚታየው ትርፍ ቀጣይነት ላይኖረው እንደሚችል ስጋታቸውን በመናገር ላይ ናቸው።
የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ መናር፣ የምርቶች ዋጋ መጨመር እና ሌሎች ምክንያቶች የሰዎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ፍላጎት ሊቀንሱ እንደሚችሉም ተገልጿል።