አሜሪካ ኮንግረሱን ሳታጸድቅ ለእስራኤል አስቸኳይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ፈቀደች
የመብት ተሟጋቾች ግን አሜሪካ እስራኤል የንጹሃንን ግድያ እንድትቀንስ ከምታደርገው ጫና ጋር አይጣጣምም በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል
ባለፈው ጥቅምት ወር ድንበሯን ጥሶ ጥቃት ያደረሰባትን ሀማስን ከምድረገጽ ለማጥፋት ያቀደችው እስራኤል በጋዛ መጠነሰፊ ጥቃት ማካሄዷን ቀጥላለች
አሜሪካ ኮንግረሱን ሳታጸድቅ ለእስራኤል አስቸኳይ የጦር መሳሪያል ሽያጭ ፈቀደች።
የባይደን አስተዳዳር ኮንግረሱን ሳያስመረምር እና ሳያጸድቅ ያለውን አስቸኳይ ስልጣን በመጠቀም ለእስራኤል 14ሺ የታንክ ሼል ሽያጭ መፍቀዱን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) ቅዳሜ እለት ገልጿል።
ፔንታጎን እንደገለፈው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 106 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን የታንክ ሸሎች በአስቸኳይ ለእስራኤል ለማቅረብ የ'አርምስ ኤክስፖርት ኮንትሮል አክት ኢመርጀንሲ ዲክላሬሽን'ን ተጠቅሟል።
ታንኮቹ ለእስራኤል ይሸጣል የተባለው ግዙፍ የጦር መሳሪያ ሽያጭ አካል መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሽያጩ በጋዛ ጦርነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ላሉት የእስራኤል ማርካቫ ታንኮች የሚሆኑ 45ሺ ሼሎችን ጨምሮ 500 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ያካታትታል።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት እየተፋፋመ መሄዱ የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ ጥያቄ ቢያስነሳም፣ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለእስራኤል በሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ ላይ ቅደመ ሁኔታ አለመቀመጡን ተናግረዋል።
የመብት ተሟጋቾች ግን አሜሪካ እስራኤል የንጹሃንን ግድያ እንድትቀንስ ከምታደርገው ጫና ጋር አይጣጣምም በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት እስራኤል አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ህግን እንድታከብር እና በንጹሃን ላይ ጉዳት እንዳታደርስ መጠንቀቅ አለባት ብለዋል።
ባለስልጣናቱ የጦር መሳሪያ ሽያጩ ለእስራኤል ራሷን የመካላከል አቅም ያሳድጋል ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለእስራኤል የሚደረገው አስቸኳይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ማለታቸውን ፔንታጎን ጠቅሷል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ድንበሯን ጥሶ ጥቃት ያደረሰባትን ሀማስን ከምድረገጽ ለማጥፋት ያቀደችው እስራኤል በጋዛ መጠነሰፊ ጥቃት ማካሄዷን ቀጥላለች።
በጦርነቱ እስካሁን 18ሺ ገደማ ፍልስጤማውን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።