ኳታር በአውሮፓ ህብረት አባላት ላይ እየተደረገ ያለውን የሙስና ምርመራ ተቃወመች
ምርመራው በኳታር-አውሮፓ ህብረት ግንኙነት አሉታዊ ተጽእኖ ሚፈጥር ነው ብላለች ኳታር
ተፈጸመ የተባለው ወንጀል በፓርላማው ታሪክ ከተከሰቱት የሙስና ቅሌቶች አንዱ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል
ኳታር፤ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ጉቦ ሰጥታለች በሚል በህብረቱ አባላት እየተደረገ ያለውን የሙስና ምርመራ ተቃወመች፡፡
ምርመራው በኳታር-አውሮፓ ህብረት ግንኙነት እንዲሁም በተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላልም ብላለች፡፡ የኳታር ዲፕሎማት በሰጡት መግለጫ የቤልጂየም ባለስልጣናትን "የተሳሳተ" መረጃ ጥቅም ላይ እያዋሉ ነው ሲሊ ተችተዋል፡፡
ዲፕሎማቱ "እየተካሄደ ያለው ምርመራ ቀጠናዊ፣ ዓለም አቀፋዊ የጸጥታ ትብብርን እንዲሁም በዓለም አቀፍ የኢነርጂ ደህንነት ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶችን አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል" ብለዋል፡፡
“ከመንግስታችን ከስነ ምግባር ጉድለት ጋር የሚያያይዘውን ውንጀላ በጥብቅ እንቃወማለን” ሲሉ መናገራቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቤልጂየም አቃቤ ህግ ኳታር ለህብረቱ ባለስልጣናት ሰጥታዋለች የተባለውን 1 ሚሊዮን ዩሮ መያዙን ተከትሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የገለጸው በሳለፍነው ሳምንት እንደነበር፡፡
ተፈጸመ የተባለው ወንጀል በፓርላማው ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት የሙስና ቅሌቶች አንዱ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።
የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤታ ሜትሶላ “ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ለምርመራው አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች እንዳይጠፉ በሚልም የ10 የፓርላማ አባላት የትኛውንም የኢሜይልና ሌሎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መረጃዎቻቸውን እንዳያዩ ታግደዋል።
በቤልጂየም ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት አራቱ ተጠርጣሪዎች "በወንጀለኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ፣ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና በሙስና ወንጀል" ክስ እንደተመሰረተባቸው አቃቤ ህግ የዛሬ ሳምንት በሰጠው መግለጫ ገልጿል።
በዚህም ለስምንት ዓመታት የህብረቱ የፓርላማ አባል የሆኑት ኢቫ ካይሊ በፖርላማው ፕሬዝዳንት ሜሶላ ከስራቸው ታግደዋል፡፡