በኳታር በስታዲየሞች ግንባታ እና በቤት ሰራተኝነት የሚሰሩ የውጭ ዜጎች ለሞት ጭምር እየተዳረጉ ነው ተብሏል
በኳታር በሚገኙ የውጭ ሀገር ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው በደል ከማሰቃየት ፣ ደሞዝ እና የዕረፍት ፈቃድ ከመከልከል አልፎ በመሳሪያ እስከመምታት መድረሱ ተገለጸ፡፡
በ2022 በኳታር ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የሚያስተናግዱ ስታዲየሞች ግንባታ ላይ የሚሰሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በተደጋጋሚ እየገለጹ ነው፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ አንድ የኳታር ዜጋ ለሥራ የመጣ የሌላ ሀገር ዜጋን በጥይት መግደሉ በሀገሪቱ ምን ያህል የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳለ ያሳያልም ተብሏል፡፡
አንድ የኳታር ዜጋ አንድ ሕንዳዊ ሠራተኛን ፊቱን በጥይት መምታቱ እና ጥቃት የደረሰበት ግለሰብ በአሁኑ ጊዜ ለሁለት ዓመት ያህል ወደ ቤተሰቡ መመለስ አለመቻሉን ዘ ናሽናል ዘግቧል፡፡ ይህም በኳታር ውስጥ ከሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል አንደኛው ነው ተብሏል፡፡
የዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች ኳታር ውስጥ የሚገጥሟቸው ችግሮች በተደጋጋሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጋለጡ ናቸው፡፡
ኳታር በመካከለኛው እና በምስራቅ እስያ የሚገኙ ሀገሮችን ዜጎች ጉልበት በመበዝበዝም ትታወቃለች፡፡ ከእነዚያ ሀገራት የሚመጡ ሰራተኞችን የሰባዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሟን እስካሁን አላቆመችም ነው የተባለው፡፡
ይፈዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኳታር ውስጥ ያሉት አጠቃላይ ስደተኞች ቁጥር ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሲሆን ባንግላዴሽ ፣ ኔፓል እና ህንድ ደግሞ ብዙውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ ከተለያዩ ሀገራት የሄዱ 173 ሺህ ሴቶች በኳታር በሰራተኛነት የሚሰሩ ሲሆን ግማሾቹ በግል ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ናቸው፡፡