በቀጣዮቹ ቀናት ሴኔጋል ከኔዘርላንድና እንግሊዝ ከኢራን የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
ተወዳጁ የዓለም ዋንጫ ነገ በኳታር ዶሀ ይጀመራል።
በአራት ዓመት አንዴ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ዘንድሮ በኳታር አዘጋጅነት ይካሄዳል።
ውድድሩ ሁልጊዜ ሰኔ ወር ላይ ተጀምሮ ሀምሌ ላይ የሚጠናቀቅ ቢሆንም ዘንድሮ ግን በሙቀት ምክንያት ወደ ህዳር ተራዝሟል።
የ2022 ዓለም ዋንጫ ከነገ ህዳር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ታህሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ የውድድር መርሀ ግብሩ ያስረዳል።
ሴኔጋል፣ ካሜሩን፣ ቱኒዝያ፣ ሞሮኮ እና ጋና አፍሪካን ወክለው በዓለም ዋንጫው ላይ ይሳተፋሉ።
ይህ ውድድር ነገ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በአዘጋጇ ኳታር እና በላቲን አሜሪካዋ ኢኳዶር መካከል ይካሄዳል።
በውድድሩ መክፈቻ እለት አንድ ጨዋታ ብቻ ይካሄዳል የተባለ ሲሆን በማግስቱ ሰኞ አፍሪካዊቷ ሴኔጋል ከኔዘርላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ ይጠበቃል።
እንዲሁም ሌላኛው ተጠባቂ የሰኞ ውድድር በእንግሊዝ እና ኢራን መካከል የሚካሄድ ሲሆን በመቀጠል አሜሪካ ከዌልስ በዚሁ ቀን እንደሚጫወቱ የውድድር መርሀ ግብሩ ያስረዳል።
ማክሰኞ ደግሞ ሜክሲኮ ከፖላንድ የሚያሰርጉት ጨዋት ተጠባቂ ሲሆን አርጀንቲና ከሳውዲ አረቢያ እንዲሁም ዴንማርክ ከቱኒዝያም ይጫወታሉ።
ኳታር ለዚህ ውድድር ሰባት ስታዲየሞችን የገነባች ሲሆን በቀን ሶስት ጨዋታዎች እንደሚደረጉ ተገልጿል።
በአለም ዋንጫው ላይ አፍሪካን ወክለው እየተሳቱፉ ያሉት አምስቱም ብሄራዊ ቡድኖች በአፍሪካዊያን አሰልጣኞች መመራታቸው ሌላኛው የውድድሩ ገጠመኝ ሆኗል።
የሴኔጋሉ ሳዲዮ ማኔ መጎዳት፣ የኳታር አልኮል እንዳይሸጥ መከልከል፣ የክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻ ዓለም ዋንጫ መሆኑ እና ውድድሩ ህዳር ላይ መደረጉ የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ክስተቶች ናቸው።