ሩሲያ ቁርዓንን አቋጥሏል ያለችውን ሰው በ14 ዓመት እስር ቀጣች
ግለሰቡ የ20 ዓመት ወጣት ሲሆን ቁርዓንን ሲያቃጥል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልን በማህበራዊ ሚዲያ ለቋል ተብሏል
ግለሰቡ ድርጊቱን የፈጸመው በሩሲያ የህዝብ ቁጣ ለመቀስቀስ በሚል እንደሆነ ተገልጿል
ሩሲያ ቁርዓንን አቋጥሏል ያለችውን ሰው በ14 ዓመት እስር ቀጣች።
ኒኪታ ዙራቭል የተባለው የ20 ዓመት ወጣት ሲሆን ከአንድ ዓመት በፊት በእስልምና ዕምነት ትልቅ ቦታ ያለው ቁርዓንን ሲያቃጥል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርቷል።
ድርጊቱ በወቅቱ የእምነቱን ተከታዮች ጨምሮ በርካቶችን ያስቆጣ ሲሆን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
በሩሲያዋ ቮልጎግራድ ክልል የሚኖረው ይህ ወጣት ወንጀሉን የፈጸመው ከዩክሬን ደህንነት ጋር ግንኙነት በመፍጠር እንደሆነ የሀገሪቱ ምርመራ ቢሮ አስታውቋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ዙራቭል ቁርዓንን ሲያቃጥል የሚያሳየውን ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያጋራው በሩሲያ አለመረጋጋት እንዲከሰት በሚል የፖለቲካ ፍላጎት ነው።
ዙራቭል ቁርዓንን ፊት ለፊቱ ካለ አንድ መስጅድ ፊት ለፊት አቃጥሏል የተባለ ሲሆን ከድርጊቱ ጀርባ የዩክሬን ደህንነቶች እንዳሉበትም ተገልጿል።
ግለሰቡ በተመሰረተበት ክስም የ14 ዓመት እስር የተላለፈበት ሲሆን ይግባኝ የመጠየቅ ፍላጎት ይኑረው አይኑረው በዘገባው ላይ አልተጠቀሰም።
እንደ ሩሲያ ደህንነት መረጃ ከሆነ ግለሰቡ ቁርዓንን ከማቃጠሉ በፊት የሩሲያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ፎቶዎችን በማንሳት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ያጋራ ነበርም ተብሏል።