የብሪታኒያን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመተካት ከሚፎካከሩት እጩዎች መካከል አራት ብቻ ቀሩ
ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን ለመልቀቅ የተገደዱት በገዥው የወግ አጥባቂ ፓርቲ ድጋፍ ካጡ በኋላ ነው
የብሪታንያ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ፉክክሩን በ115 ድምጽ እየመሩ ነው
ጠንካራ ፉክክር እያስተናገደ ባለው የብሪታኒያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን የመተካት ፉክክር አራት እጩዎች ቀርተዋል፡፡
የብሪታንያ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ቀጣዩ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በሚደረገው ውድድር መሪነቱን ይዘዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመተካት በርካታ እጩዎች ቀርበው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የቀሩት አራት ተፎካካሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
ሱናክ ሰኞ እለት በተካሄደው ሶስተኛው የወግ አጥባቂ ህግ አውጭዎች ድምጽ 115 ድምጽ ሲያገኙ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ፔኒ ሞርዳውንትን በ82 እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስን በ71 ድምጽ በልጠው ነው፡፡
ቦሪስ ጆንሰን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ቅሌት የበዛበት አስተዳደራቸው በገዥው ወግ አጥባቂ ፓርቲ ውስጥ የብዙዎችን ድጋፍ ካጣ በኋላ እሳቸውን እንደሚለቁ በመግለጽ፣ እሳቸውን ለመተካት የሚደረገው ሩጫ አስቀያሚ ለውጥ ፈጥሯል፡፡ በርካታ ተፎካካሪዎች ፊታቸውን ፉክክሩን እየመሩ ወዳሉት ሱናክ ላይ አዙረዋል።
የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቶም ቱገንድሃት የቀድሞ ወታደር እና በመንግስት ውስጥ ምንም አይነት ሚና ያልነበራቸው የጆንሰን ተቺ በትናንቱ ድምጽ በ31 ድምጽ በማግኘታቸው ሰኞ ዕለት ከአመራር ዉድድሩ ተወግደዋል።
የቀድሞ የእኩልነት ሚኒስትር ወይዘሮ ኬሚ ባደናች 58 ድምፅ በማግኘት አራተኛ ሆናለች።
የገዢው ወግ አጥባቂ ፓርቲ 358 የሕግ አውጭዎች በዚህ ሳምንት ውድድሩን እስከ መጨረሻው ያሽከረክራሉ፤ በእያዳንዳንዱ ዙር ትንሽ ድምጽ ያገኘውን እጩ ያስወግዳሉ፡፡ የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ 200,000 አባላት በበጋው ወቅት የፖስታ ድምጽ ከሰጡ በኋላ በፈረንጆቹ መስከረም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይገለጻል፡፡
ጆንሰን ስልጣን ይልቀቁ የሚል የበረታ ጫና ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጭምር ሲደረግባቸው የቆየ ሲሆን በመጨረሻም በስልጣናቸው ሊቀጥሉ ባለመቻላቸው እንዳዘኑ ለምክር ቤት አባላቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት በሀገሪቱ የታወጀውን የኮሮና ቫይረስ ድንጋጌዎች በመጣሳቸው ከስልጣን እንዲለቁ ተጠይቀው የነበረ ቢሆንም ተደጋጋሚ ጥፋቶችን አጥፍተዋል ለሌሎች አርዓያ መሆን አይችሉም በሚል ግፊት ሲደርግባቸው መቆየቱ ይታወሳል፡፡