የብሪታኒያ መንግስት በሞ ፋራህ ዜግነት ጉዳይ ምን አለ?
ይህን ንግግሩን ተከትሎ ዜግነቱን ሊያጣ ይችል ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል
ሞ ፋራህ ታዳጊ እያለ በአንዲት በማያውቃት ሴት ተገዶ ከጅቡቲ ወደ ብሪታንያ መግባቱን መናገሩ ይታወሳል
የኦሎምፒክ ሻምፒኑ ትክክለኛ መጠሪያ ስሙ ሞ ፋራህ እንዳይደለና ትክክለኛ ስሙ ሁሴን አብዲ ካሂን እንደሆነ ከቢቢሲ ዶክመንታሪ ጋር በነበረው ቆይታ መናገሩን ተከትሎ የብሪታኒያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የወሰደው እርምጃ አለመኖሩ “ሰላም አግኝቻለሁ” ሲል ተናገረ፡፡
ሞ ፋራህ ታዳጊ እያለ በአንዲት በማያውቃት ሴት ተገዶ ከጅቡቲ ወደ ብሪታንያ በህገ ወጥ መንገድ መግባቱን መናገሩ አይዘነጋም፡፡
እንደ አትሌቱ ገለጻ ከሆነ ገና የ8 ወይ የ9 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው በአንዲት አይቷት እንኳን በማያውቅ ሴት አስገዳጅነት ከጅቡቲ ወደ ብሪታኒያ የገባው፡፡
መሀመድ ፋራህ የሚል ስም ተሰጥቶት ወደ ብሪታኒያ እንዲገባና ባመጣችው ሴት ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ልጆችን እንዲንከባከብ መደረጉንም ዛሬ ረቡዕ ለእይታ እንደሚበቃ ለተነገረለትና "እውነተኛው ሞ ፋራህ" በሚል ለተዘጋጀው የቢቢሲ ቲቪ ዘጋቢ ፊልም ተናግሯል ።
የሞ ፋራህ ለዓመታት ደብቆት የቆየውን አነጋጋሪ እውነታ ለቢቢሲ መናገሩን ተከትሎ የብሪታኒያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እርምጃ መውሰዱ አይቀሬ ነው የሚል የበርካቶች ግምት የነበረ ቢሆንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግን ያልተጠበቀ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የሞ ፋራህን ጉዳይ ወደ ማጣራት የሚገባበት ምንም ምክንያት እንደሌለም ነው ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፡፡
ለዚህ እንደ ምክንያት ያቀረበው ደግሞ ከህግ አንጻር ሰዎች ባልተገባ መንገድ ዜግነት ማግኘታቸው ከተረጋገጠ መንግስት ዜግነታቸው የመሰረዝ ስልጣን ቢኖረውም “ህጻናት ተታለው ዜግነት በሚያገኙበት ሂደት አዋቂዎች እንጅ ህጻናት ራሳቸው ተባባሪ መሆን አይችሉም” የሚል ነው፡፡
በዚህም ፋራህ ከቢቢሲ ራድዮ 4 ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ፤ የዜግነት ጉዳዮችን የሚከታተለው የብሪታኒያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ “ሰላም አግኝቻለሁ” ሲል የተሰማውን የህሊና እረፍት ገልጿል፡፡
“ይህቺ (ብሪታኒያ) ሀገሬ ናት፣ የሰውነት ማጎልመሻ መምህሬ አለን እንዲሁም በልጅነት እድሜዬ ድጋፍ ያደረጉልኝ ሁሉም ሰዎች አጠገቤ ባይኖሩ ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻልኩም ነበር” ብሏል፡፡
“በህይወት ዘመኔ ውለታ የዋሉልኝ አያሌ ሰዎች አሉ፤ በተለይም ባለቤቴ ለሙያዬ አጋዥ ሚና ነበራት፤ ስለጉዳዩ እንዳወራ ያደፋፈረችኝና ያለፈ ታሪኬ ምንም እንዳልሆነ የነገረችኝ እሷ ናት” ሲልም አክሏል ፋራህ።
ሞ ስለ ማንነቱ መናገሩን ተከትሎ እየጎረፉለት ያሉትን አስተያየቶች እና ምላሾች “የሚያስደንቁ” ናቸው ሲል ገልጿቸዋል፡፡
“ስለዚህ ጉዳይ ከቤተሰቦቼ ጋር ለማውራት እንኳን ምቾት አይሰጠኝም ነበር ፤ አዚህ ለመድረስ ረዥም ጊዜያት ፈጅቶብኛል ነገር ግን ሰዎች ስላሳለፍኩት ህይወት እንዲያውቁ የሚረዳ ዘጋቢ ፊልም መሰራቱ ደስተኛ ነኝ” ሲል ስሜቱን ገልጿል።
ባለቤቱ በበኩሏ ያለፈውን የሞ ፋራህ ታሪክ ከሰማች በኋላ “የተደበላለቁ ስሜቶች” እንደፈጠረባት ተናግራለች።
“መጀመሪያ የተሰማኝ ከባድ ሀዘን እና ድንጋጤ ነበር፤ የ9 ዓመት ሞ ፋራህ ነበር እየመጣ ፊቴ ላይ ድቅን የሚለው፤ ከዚህ ባልተናነሰም እንደዛ ባደረጉት ሰዎች ንዴት ይሰማኝ ነበር” ስትልም ነው የሞ ፋራህን ትክክለኛ ማንነት ስታውቅ የነበራት ስሜት የገለጸችው፡፡
ብሪታኒያን በአትሌቲክሱ ያስጠራው የሎንደን እና የሪዮ ኦሎምፒኮች የ5 ሺ እና የ10 ሺ ርቀቶች ሻምፒዮናው ሞ "ሰር" የሚል ማዕረግን ከንግስት ኤልሳቤጥ እስከማግኘት መድረሱ ይታወቃል፡፡