የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን እንደሚለቁ ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንደሚለቁ ያሳወቁት ከፓርቲያቸው ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው በኋላ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ በሚቀጥለው ሳምንት ለተተኪያቸው ስልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን እንደሚለቁ ገለጹ፡፡
ቁልፍ የስልጣን አጋሮቻቸውን ጭምር ያጡት፤ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አጣብቂኝ ውስጥ በመግባታቸው ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ገልጸዋል፡፡
ጆንሰን ስልጣን ይልቀቁ የሚል የበረታ ጫና ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጭምር ሲደረግባቸው የቆየ ሲሆን በመጨረሻም በስልጣናቸው ሊቀጥሉ ባለመቻላቸው እንዳዘኑ ለምክር ቤት አባላቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሁን ቀደም ፈጽመዋቸዋል ከተባሉ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ጋር በተያያዘ ስልጣን እንዲለቁ ጫናዎች ሲደረጉ ነበር፡፡
መተማመን ተስኖናል ያሉ ባለስልጣናት መበርከታቸውን ተከትሎ በቅርቡ በስልጣን ይቀጥሉ በሚለው ላይ በምክር ቤት አባላት የመተማመኛ ድምጽ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
45 በመቶ ያህል የምክር ቤቱ አባላት ድጋፋቸውን ባልሰጡበት በመተማመኛ ድምጹም ጆንሰን ከስልጣን ከመሰናበት ለጥቂት ተርፈውም ነበር፡፡
ሆኖም ከሚመሩት ወግ አጥባቂ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮቻቸው ጭምር የሚቀርበው ጥያቄ መበርታቱን ተከትሎ ጆንሰን ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ብቻም ሳይሆኑ አብረን ለመቀጠል አንችልም በሚል በራሳቸው ፈቃድ ስልጣን የሚለቁ የካቢኔ አባላቶቻቸውም በርክተው ነበር፡፡
ለዚህም ትናንት ስልጣን መልቀቃቸውን በይፋ ያሳወቁትን የጤና ሚኒስትሩን ሪሺ ሱናክን ጨምሮ የቀድሞው የጤና ሚኒስትር ጃቪድ ሳቪድ እንዲሁም ሌሎች 22 ባለስልጣናት ማሳያ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም በግምጃ ቤት ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ቻንሰለር ሪሺ ሱናክ በራሳቸው ፈቃድ ስልጣን ከለቀቁ ከፍተኛ የሃገሪቱ መንግስትና የወግ አጥባቂ ፓርቲ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን በሚቀጥለው ሳምንት ስልጣን ስለሚያስረክቡበት ሁኔታ ዝርዝር እቅዳቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ የተናገሩ ሲሆን ስልጣናቸውን ለተተኪው እስከሚያስረክቡ ድረስ ብቻ በስልጣን ላይ እንደሚቆዩም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት በሀገሪቱ የታወጀውን የኮሮና ቫይረስ ድንጋጌዎች በመጣሳቸው ከስልጣን እንዲለቁ ተጠይቀው የነበረ ቢሆንም ተደጋጋሚ ጥፋቶችን አጥፍተዋል ለሌሎች አርዓያ መሆን አይችሉም በሚል ግፊት ሲደርግባቸው ቆይቷል፡፡