የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ፍላጎት ያሳዩ ፖለቲከኞች 11 ደረሱ
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን እንደሚለቁ ማሳወቃቸው ይታወሳል
የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ምትክ ከ2 ወር በኋላ ይታወቃል ተብሏል
ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት ወደ ውድድር የመጡ የብሪታኒያ ፖለቲከኞች ቁጥር 11 መድረሱ ተነግሯል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በተደጋጋሚ የሀገሪቱን ህጎች ጥሰዋል በሚል ስልጣን እንዲለቁ የበረታ ጫና ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጭምር ሲደረግባቸው ቆይቶ በመጨረሻም ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ባሳለፍነው ሳምንት መናገራቸው ይታወሳል።
መተማመን ተስኖናል ያሉ ባለስልጣናት መበርከታቸውን ተከትሎ በቅርቡ በስልጣን ይቀጥሉ በሚለው ላይ በምክር ቤት አባላት የመተማመኛ ድምጽ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
ቁልፍ የስልጣን አጋሮቻቸውን ጭምር ያጡት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አጣብቂኝ ውስጥ በመግባታቸው ስልጣናቸውን እንደሚለቁ እና በቀጣይ ስልጣናቸውን ለተተኪው እንደሚያስረክቡም ገልጸዋል፡፡
ይሄንን ተከትሎም በርካታ የብሪታኒያ ፖለቲከኞች ቦሪስ ጆንሰንን ተክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ፍላጎታቸውን በማሳወቅ እና እንዲመረጡ ቅስቀሳዎችን በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡
እስከዛሬ ድረስም 11 የወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ፍላጎታቸውን ገልጸው ቢመረጡ ምን ምን ማስተካከያዎችን እንደሚያደርጉ በተለያዩ መንገዶች በመናገር ላይ ናቸው፡፡
ብሪታኒያን በመምራት ላይ ያለው የወግ አጥባቂ ፓርቲ ቦሪስ ጆንሰንን በመተካት ቀጣዩ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች እንዲያመለክቱም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ፓርቲው እንዳሳወቀው እስከ ነገ ድረስ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የመወዳደር ፍላጎት ያላቸው አካላት እንዲያመለክቱ ገልጾ በሚቀጥለው ሳምንት ማለትም ከ10 ቀን በኋላ ሁለት የመጨረሻ እጩ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ለምርጫ ካቀረበ በኋላ መስከረም ወር ላይ የቦሪስ ጆንሰን ምትክ የሚታወቅ ይሆናል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በስልጣን ላይ ያለው የብሪታኒያው ወግ አጥባቂ ፓርቲ በፈረንጆቹ 1922 ላይ ባወጣው የምርጫ ህግ የመጨረሻዎቹ ሁለት እጩ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ምርጫ በሚስጢር በፖስታ ቤት በሚሰጥ ድምጽ ይወሰናል፡፡