የዘር መድሎን የሚቃወሙ አክቲቪስቶች የአሜሪካን ፖሊስ ከሰው ረቱ
አክቲቪስቶቹ በድምሩ የ14 ሚሊዮን ዶላር ካሳ አግኝተዋል

አክቲቪስቶቹ ክሱን የመሰረቱት በፈረንጆቹ 2020 ነበር
የዘር መድሎን የሚቃወሙ አክቲቪስቶች በአሜሪካ ደንቨር በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ላይ ክስ መስርተው ረትተዋል፡፡
አክቲቪስቶቹ፤ክሱን መስርተው የነበረው የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ በተዘጋጀ ሰልፍ ላይ ፖሊስ ከመጠን ያለፈ ኃይል እንደተጠቀመ በመግለጽ ነበር፡፡ በ2020 በአሜሪካ ፖሊሶች የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ ጉዳይ በርካቶች አስቆጥቶ አደባባይ አሰባስቦ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም የዘር መድሎን ሚቃወሙ አክቲቪስቶች የደንቨር ፖሊሶች በሰልፈኞች ላይ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅመዋል የሚል ክስ አቅርበዋው ነበር፡፡
የአክቲቪስቶቹና የፖሊሶቹ የክስ ሂደት የተጀመረው ሰኔ 2020 ነበር፡፡ የአካባቢ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የደንቨር ፖሊስ በከፍተኛ ኦፊሰር ካልተፈቀደ በስተቀር በጊዜያዊነት አስለቃሽ ጭስ፣ የፕላስቲክ ጥይትና ሌሎችንም እንዳይጠቀም ከልክሎት ነበር፡፡
የጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ አባል መገደል ደንቨርን ጨምሮ በመላው አሜሪካ ጥቁሮች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡ በተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ፖሊስ ያልተገባና ያልተመጣጠነ ኃይል በመጠቀሙ ምክንያት ክስ የቀረበበት ሲሆን በክሱም የደንቨር ፖሊስ ተረቷል፡፡
በዚህም መሰረት ክሱን የመሰረቱት የዘር መድሎን የሚቃወሙ አክቲቪስቶች 14 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ አግኝተዋል፡፡ ክሱን ረተው ከፍተኛ ገንዘብ ካገኙት መካከል በፖሊስ የተመታው ዛካሪ ፓካርድ 3 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡
ግለሰቡ ከፖሊስ በደረሰበት ጥቃት ጭንቅላቱና መንጋጋው እንዲሁም አንጎሉ መጎዳታቸው ተገልጿል፡፡ የደንቨር ሕዝብ ደህንነት ባወጣው መግለጫ እንዳለው ፖሊሶቹ ስህተት መስራታቸውን ገልጿል፡፡