“ባንስማማበትም የፍርድ ቤቱን ብይን እናከብራለን”- ራይላ ኦዲንጋ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የፊታችን መስከረም 3 ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ኦዲንጋ የፍርድ ቤቱን ውጤት በጸጋ መቀበላቸው አድንቀዋል
የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኬንያ በተካሄደው ፕሬዝዳናታዊ ምርጫ የዊሊያም ሩቶ አሸናፊነትን ያጸናበት የመጨረሻ ብይን ይፋ አድርጓል፡፡
ምርጫውን ተከትሎ ተፎካካሪ ዕጩ የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ በምርጫው ሂደት ላይ ማጭበርበር መከሰቱን በመግለጽ ያቀረቡትን ክስ ተከትሎ ነው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው።
ሰባት አባላት ያሉት የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበለትን ክስ ሲመለከት ቆይቶ ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ አምስተኛው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡበት ሂደትን ተቀብሎታል።
በምርጫው ጠባብ በሆነ ውጤት የተሸነፉትና ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ሲከራከሩ የቆዩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋም ውጤቱ በጸጋ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል፡፡
ራይላ ኦዲንጋ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “ባንስማማበትም የፍርድ ቤቱ የዛሬ ብይን እናከብራለን” ብለዋል፡፡
እኛ ሁሌም ለህግ የበላይነት እና ለህገ መንግስቱ መከበር የቆምን ነንም ነው ያሉት ራይላ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት፤ በዊልያም ሩቶ መመረጥ መደሰታቸው እንዲሁም በራይላ ኦዲንጋ የፍርድ ቤቱን ውጤት በጸጋ መቀበል ደስታ እንደተሰማቸው በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፋቸው ገልጸዋል፡፡
በኬንያ ህግ መሰረት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሪቱ የፊታችን መስከረም 3 ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ኬንያ ያካሄደችው ምርጫ ከዝግጅቱ ጀምሮ ጠንካራ የሚባልና የምርጫ አስተዳደር አፈጻጸሙ በሁሉም መመዘኛዎች ጥሩ ሚባል እንደነበር በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተመራው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ከምርጫ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማስተናገድ እና የህዝብን እምነት በማሳደግ እስከ ምርጫው ቀን ድረስ የፍትህ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ገልጸዋል የኢጋድ ታዛቢ ቡድን መሪው ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ።
ከተመለከትናቸው ጉዳዮች አንዱ በእጅ መመዝገቢያ አጠቃቀምን በተመለከተ የፍተህ አካላት የነበራቸው ሚና ነው ያሉት ዶ/ር ሙላቱ፤ በኬንያ ዲሞክራሲን ከማጠናከር አንጻር የኬንያ የፍትህ አካላት በህዝብ ያላቸውን ተአማኒነት እንደ ተጨባጭ ስኬት እንቆጥረዋለንም ሲሉም ተናግረዋል።