ራይላ ኦዲንጋ ምርጫውን እንዳሸነፉ እርግጠኛ እንደሆኑና በፍርድ ቤት አስወስነው ሀገሪቱን መምራት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፍርድ ቤት ክርክር ነገ ይጀመራል።
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከሁለት ሳምንት በፊት የተካሄደ ሲሆን፤ ላለፉት አምስት ዓመታት ኬንያን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ዊሊያም ሩቶ ምርጫውን ማሸነፋቸው ይታወሳል።
በዚህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለ5ኛ ጊዜ በዕጩነት የቀረቡት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።
ራይላ ኬንያን በፕሬዝዳነትንት ለመምራት 5 ጊዜ በዕጩነት ቢቀርቡም ለአምስተኛ ጊዜ ያልተሳካላቸው ሲሆን ከምርጫው ውጤት መገለጽ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል።
ራይላ ኦዲንጋ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውጤት ተቀባይት እንደሌለውና እርሳቸውም እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
በፓርቲያቸው የሚዲያ ክፍል በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ውጤቱ ተቀባይነት የለውም በሚል የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫውን ውጤት ውድቅ እንዲያደርግ እና የእሳቸውን አሸናፊነት እንዲያውጅ ጠይቀዋል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ክርክሩን በነገው ዕለት መስማት እንደሚጀምር የኬንያው ሲቲዝን ሚዲያ ዘግቧል።
ራይላ ኦዲንጋ በዛሬው ዕለት እንደተናገሩት ምርጫውን እንዳሸነፉ እርግጠኛ እንደሆኑ እና በፍርድ ቤት አስወስነው ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት መምራት እንደሚጀምሩ አክለዋል።
የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን በናይሮቢ ባሉ አራት ምርጫ ጣቢያዎች ከህትመት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ስህተት ምርጫው እንዳይካሄድ የወሰነ ሲሆን ራይላ ኦዲንጋ በዚህ ትልቅ ቅሬታ እንዳላቸው ተናግረዋል።
22 ሚሊዮን ኬንያዊያን የተሳተፉበት የዘንድሮው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ዊሊያም ሩቶ 50 ነጥብ 49 የሚሆነውን የመራጮች ምርጫ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል መባሉ ይታወሳል።