ድርቅ በተከሰተባቸው የቦረና ዞን ወረዳዎች ዝናብ መጣሉ ተገለጸ
በዞኑ ዝናብ መጣል የጀመረው ባለፈው ሃሙስ እለት ጀምሮ ነው ተብሏል
በቦረና ዞን የሚገኙት 13ቱም ወረዳዎች መጠኑ የተለያየ ዝናብ ማግኘታቸውን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል
በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ ካጋጠማቸው ቦታዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የቦረና ዞን አንዱ ነው፡፡ከወራት ወራት በኋላ በቦረና ዞን በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ከሰሞኑ ዝናብ መጣሉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡
የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናሩት በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ዝናብ መጣሉን ተናግረዋል፡፡ ከሃሙስ ዕለት ጀምሮ ዝናብ መጣሉን ያነሱት አቶ ጃርሶ በዚህም ነዋሪዎች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሃሙስ ዕለት ጀምሮ በቦረና ዞን በሚገኙ 13ቱም ወረዳዎች የተለያዩ መጠን ያለው ዝናብ መጣሉንም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ መጠን ያለው ዝናብ በዞኑ መመዝገቡን ያነሱት አቶ ጃርሶ በዚህም ኩሬዎች ውኃ መያዛቸውን፣ ውኃ መገኘቱንና ለሕብረተሰቡ ተስፋ መስጠቱን ነው የተናገሩት፡፡
ከፍተኛ ዝናብ ያገኙት አካባቢዎች ያቤሎ ወረዳ እና ያቤሎ ዙሪየ የሚገኙ ቀበሌዎች እንደሆኑም አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል፡፡ ምንም እንኳን በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ዝናብ ቢጥልም በሁሉም ቀበሌዎች ላይ ግን ዝናብ አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
በቦረና ዞን 13 ወረዳዎች ያሉ ሲሆን በነዚህ ወረዳዎች ደግሞ 212 ቀበሌዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዘኒህ ቀበሌዎች መካከል 38 ቱ ዝናብ አለማግኘታቸውን አቶ ጃርሶ አንስተዋል፡፡
በድርቅ ላይ የቆዩት የቦረና ዞን ወረዳዎችና ቀበሌዎች በዝናቡ እፎይታ ቢያገኙም ጉዳት ማስከተሉም ተገልጿል፡፡ ከሰሞኑ የዘነበውን ዝናብ ድርቅ ላይ የቆዩት እንስሳት መቋቋም እንዳልቻሉት አቶ ጃርሶ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ እስካሁን 13 ሺ ከብቶች እና ፍየሎች መሞታቸውን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ፈጣሪያቸውን በማመስገን ከብቶቻቸው የዝናብ ዉኃ ሲጠጡ የሚያሳይ ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስል ከሰሞኑ ሲዘዋወር ነበር፡፡
ሌላው ከፍተኛ የድርቅ አደጋ የተከተበት ክልል ሶማሌ ክልል ነው፡፡ የክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ፈርሃን ጅብሪል ባለፈው ጥቅምት ወር ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ድርቁ በክልሉ ከሚገኙት 11ዱ ዞኖች በ9ኙ መከሰቱን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ኃላፊው በድርቁ ምክንያት ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች ለአደጋ መጋለጣቸውንም ገልጸው ነበር፡፡
ከሰሞኑ በሶማሌ ክልልም ድርቅ ያጋጠማቸው አካባቢዎች ዝናብ እንዲያገኙ የጸሎት ስነ ስርዓት አካሂዶ ነበር፡፡
በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በተለያዩ ዞኖች ድርቅ ያጋጠመ ሲሆን በርካታ እንስሳት መሞታቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች አድርገውት በነበረው ጉብኝት በድርቅ ምክንያት “የአንድም ሰው ህይወት አልጠፋም” ማለታቸው ይታወሳል፡፡