ተመድ በሶማሌ ክልል ባለ ድርቅ ምክንያት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ ይችላሉ አለ
ተመድ ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት እሰከ 1ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል
በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ 845 ሺ ዜጎች መፈናቀላቸውንም ተመድ አስታውቋል
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ 845 ሺ ዜጎች መፈናቀላቸውንና ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዋና ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች የችግሩ መጠን እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል፡፡
“እኛ እና የሰብዓዊ እርዳታ አጋሮቻችን በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለተጠቁና 2.7 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች የምናደርገውን የምግብ እርዳታ መጠን በማሳደግ ላይ እንገኛለን”ም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ባለፈው ወር ብቻ ከ120 ሜትሪክ ቶን በላይ የህክምና እና ሌሎቸ አቅርቦቶች ድርቅ በተከሰተባቸው ቦታዎቸ ለሚገኙ ሰዎች ማዳረስ ተችሏል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ አሁንም ቢሆን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ህጻናት ለማከም የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት የህክምና ምግብ እያከፋፈሉ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ከ5 አመት በታች ከሚገኙ ህጻናት መካከል ግማሽ ያህሉ ወይም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ቃል አቀባዩ አሳስቧል።
“ከለጋሾች እና ከሌሎችም አካላት ድጋፍ ቢደረግም፤ ያለው ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋል”ም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡
ለሶማሊያ የሰብአዊ ምላሽ እቅድ በሶማሊያ ለሚገኙ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለድርቅ የተጋለጡ ሶማሊያውያንን ለመርዳት ወደ 1ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን እስካሁን የተሸፈነው 3 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው።
በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ለሶስተኛ ጊዜ የሚጠበቀው ዝናብ ባለመገኘቱ ባጋጠመው ድርቅ በአካባቢው የሚኖሩ የአርብቶ አደር እንዲሁም የአርሶ አደር ማህበረሰቦች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ /ኦቻ/ በታህሳስ ወር ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ኦቻ የሶማሌ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ቢሮን ዋቢ አድርጎ እንደገለጸው በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ ለድርቅ የተጋለጡትንና ምንም ዓይነት ምርት ያልተገኘባቸው ዞኖች ፋፋን እና ሲቲ የተባሉ ዞኖች ናቸው፡፡
ከእነዚህም መካከል እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የማሽላ እና የበቆሎ ምርት፣ ከተጠበቀው የስንዴ ምርት 30 በመቶ እንዲሁም ከታሰበው የሽንኩርት እና የቲማቲም ምርት 30 በመቶው ታጥቷል።
ድረቁን ተከትሎ በዞኖቹ ይኖሩ የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀው በርካታ አርብቶና አርሶ አደሮች ለግጦሽ ሳርና ውሃ ፍለጋ በሚል መሳደዳቸውንም ኦቻ ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል፡፡
በድርቁ ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እና የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር ባለመኖሩ በሶማሌ 99 ሺ ተማሪዎች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ 56 ሺህ ተማሪዎች በአጠቃላይ 155 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውም ተጠቁሟል።