የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ‘’በፋርምጌት ቅሌት” ስልጣናቸው አደጋ ላይ ነው
ፕሬዚዳንቱ 4 ሚሊየን ዶላር ጥሬ ገንዘብ ተሰርቀው ዝምታን መርጠዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ቆይቷል
ራማፎሳ ጥፋተኛ ከተባሉ የመተማመኛ ድምጽ ተነፍገው ከስልጣናቸው ሊነሱ እንደሚችሉ ተነግሯል
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከስልጣናቸው ሊያሳግዳቸው የሚችል ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል ተነገረ።
ፕሬዚዳንቱ ከሁለት አመት በፊት ተፈጸመ ከተባለ ወንጀል ጋር በተያያዘ ነው ክስ ሊመሰርትባቸው ነው የተባለው።
የቀድሞው የሀገሪቱ የደህንነት ሹም አርተር ፍሬዘር በፕሬዚዳንቱ ላይ ባቀረበው ክስ በየካቲት ወር 2020 የራሞፎሳ ቤት በዘራፊዎች ተበርብሮ ከ4 ሚሊየን ዶላር በላይ ጥሬ ገንዘብ ተዘርፏል።
በሊምፖፖ ክፍለ ግዛቷ ዋተርበርግ የሚገኘው ቤታቸው ሲዘርፍ ፕሬዚዳንቱ እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሸፋፍነውታል ይላል ፍሬዘር።
ዘራፊዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም ትንፍሽ እንዳይሉ ማድረጋቸውንም ይጠቅሳል።
ይህ የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን “የፋርምጌት ቅሌት” የሚል ስያሜ የሰጡት ጉዳይ አሁንም መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል።
ራማፎሳ በበኩላቸው ክሱን አይቀበሉትም። ተሰረቀ የተባለው ገንዘብ ተጋኗል፤ 580 ሺህ ዶላር ጎሽ ሸጬ ያገኘሁት ገንዘብ ተስርቋል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ጉዳዩን እና ዘራፊዎቹን ከፖሊስ ለመሰወር ጥረት አድርገዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስም አጣጥለዋል።
በቤታቸው የተዘረፈው 4 ሚሊየን ዶላር በህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና በሙስና የተገኘ ሊሆን ይችላል ያለው ፍሬዘር ክስ እንዲመሰረትባቸው ያቀረበው ማመልከቻ በተለያዩ አካላት ሲታይ ቆይቷል።
ገለልተኛ የሆነ መርማሪ ቡድን ፕሬዚዳንቱ ስልጣናቸውን ያለአግባብ መጠቀማቸውንና የጸረ ሙስና ህጉን መተላለፋቸውን የሚያሳይ ሪፖርት አውጥቷል።
የሀገሪቱ ፓርላማም ከመርማሪዎቹ የቀረበለትን ግኝት ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በመመርመር ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ክስ ይመስረትባቸው ወይስ ተጠያቂ አያደርጋቸውም የሚለውን ይወስናል።
ራማፎሳ በ2024ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኤ ኤን ሲን ወክለው ስለመወዳደራቸው ማረጋገጫ የሚያገኙት ከሳምንታት በኋላ በሚደረግ የፓርቲው ጉባጼ ነው።
የፋርምጌት ቅሌት ክሱም በፓርቲው ሊቅመንበርነት ምርጫ ላይ ጥቁር አሻራውን እንዳያሳርፍበት ተሰግቷል።
ፓርቲያቸው አፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ ለነገ የጠራው ስብሰባ ላይም ይሄው ጉዳይ እንደሚነሳ ይጠበቃል።
በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የስልጣን ዘመን ተንሰራፍቶ የነበረውን ሙስና ለማጥፋት ቃል የገቡት ሲሪል ራማፎሳ 4 ሚሊየን ዶላር በመደበቅ ተጠርጥረዋል።
ፓርላማው የሚያቋቁመው ኮሚቴ ፕሬዚዳንቱን ጥፋተኛ ሆኖ ካገኛቸው የመተማመኛ ድምጽ እንዲነፈጋቸው ድምጽ ይሰጥበታል።
ኤ ኤን ሲ አባላቱን በወንጀል ክስ ካልሆነ በሙስና ጉዳይ ጥፋተኞችን ቀጥቶ አያውቅም የሚሉ ታዛቢዎች ግን የፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መነሳት አይታሰብም እያሉ ነው።.