"አይናፋሩ" ህንዳዊ ስራ ለመልቀቅ አራት ጣቶቹን ቆርጧል
የ32 አመቱ ወጣት የግራ እጁን ጣቶች የቆረጠው ለአለቃው ስራ የመልቀቂያ አሳማኝ ማስረጃ ለማቅረብ መሆኑን አምኗል
ለፖሊስ "በሞተር ሳይክል ስጓዝ አደጋ ደርሶብኝ ጣቾቼን አጣሁ" ብሎ ያቀረበው ሪፖርት አስገራሚው ዜና እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል
ለብዙዎች ቀላል የሚመስለው "እምቢ፤ አይሆንም፤ በቃኝ" የሚል ምላሽ ለህንዳዊው ወጣት ፈተና ሆኖበት ዋጋ አስከፍሎታል።
ማዩር ታራፓራ የተባለው ግለሰብ አለቃውን ስራ መልቀቅ እፈልጋለሁ ማለት ከብዶታል። እናም አውጥቶ አውርዶ መፍትሄ ይሆናል ያለው ጣቶቹን መቁረጥ ሆነ።
የ32 አመቱ የኮምፒውተር ባለሙያ አራት ጣቶቹን ማጣቱ ስራ ማከናወን እንደማያስችለው ለአለቃው ማሳየት ብቸኛው ከስራ መልቀቂያ መንገድ ሆኖ ታይቶታል።
በጉጃራት ግዛት የሱራት ከተማ ነዋሪው የደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ያስደነገጣቸው ቤተሰቦቹ ለፖሊስ ሪፖርት እንዲያደርግ ይገፋፉታል።
"አይናፋሩ" ታራፓራ ለፖሊስ የሰጠው ቃል ግን ይሉኝታ አይሉት ፍርሃቱ አደገኛ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ እንዳደረገው አጋልጧል።
ወጣቱ "ወደ ጓደኛዬ ቤት ሞተር ሳይክል እያሽከረከርኩ ስጓዝ ድንገት ተጫጭኖኝ መንገድ ስቼ ወደቄ ራሴን ሳትኩ፤ ከ10 ደቂቃ በኋላ ስነቃ የግራ እጄ አራት ጣቶች የሉም" ሲል ነበር ቃሉን የሰጠው።
ፖሊስ የታራፓራ ጣቶች ለጥልቆላ ስራ ተቆርጠው ተወስደው ሊሆን እንደሚችል በመገመት ምርመራውን ሲቀጥል አደጋው ደርሶበታል በተባለው አካባቢ የተገጠሙ ሲሲቲቪ ካሜራዎች የቀረጿቸውን ምስሎች ደጋግሞ ተመልክቷል። ምስሎቹ ግን ታራፓራ ሞተር ሳይክሉን አቁሞ ሲወርድ እና በግራ እጁ ላይ ጉዳት ደርሶበት ሲመለስ ነው ያሳዩት።
የኮምፒውተር ባለሙያው መርማሪዎች በመስቀለኛ ጥያቄ ሲያጣድፉት እውነቱን አምኗል።
ጣቶቹን በቢላ ከቆረጠ ከ4 ቀናት በኋላ ሞተሩን አደጋው ደርሶበታል ባለው ስፍራ ላይ ማቆሙን መናገሩንም ዘ ሂንዱ ዘግቧል።
በቤተሰቦቹ የአልማዝ ኩባንያ መስራት እንደማይፈልግ ግን ይህንን መናገር እንደከበደውም ገልጿል።
የሱራት ከተማ ፖሊስ ሶስቱን የተቆረጡ ጣቶች ማግኘቱና ምርመራውም መቀጠሉን ነው ያስታወቀው።