ፊንላንድ ልክ እንደ ጎረቤቷ ስዊድን ሁሉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ለመቀላቀል ወስናለች
የሩሲያ ሁኔታ አስግቶናል ያሉ ፊንላንዳውያን በገፍ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየወሰዱ ነው ተባለ፡፡
ፊንላንዳውያኑ ልክ እንደ ዩክሬን ሁሉ የመወረር እጣ ፋንታ ሊገጥመን ይችላል በሚል የሃገሪቱን ብሔራዊ ጦር በመቀላቀል በፈቃደኝነት ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየወሰዱ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
ፊንላን ልክ እንደ ጎረቤቷ ስዊድን ሁሉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ለመቀላቀል ወስናለች፡፡ የአባልነት ማመልከቻ ደብዳቤዋን ከሰሞኑ እንደምታቀርብም ተነግሯል፡፡
ይህ ደግሞ "የማይሆን ነው" ያለችውን ሩሲያን አስቆጥቷል፡፡
ስለ ሁኔታው የተናገሩት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊንላንድ እና የስዊድን ይህን ማለት በራሱ ስጋት ሊሆን ባይችልም ጠንከር ያለ አጸፋዊ ምላሽ ሊያሰጥ እንደሚችል ግን ተናግረዋል፡፡
ሃገራቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ከሃገራቱ ወደምትጎራበትባቸው አካባቢዎች እንደምታስጠጋም ነው የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ደግሞ የደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በመስራት ላይ ያሉት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ከአሁን ቀደም የተናገሩት፡፡
ሩሲያ እና ፊንላንድ 1 ሺ 300 ገደማ ኪሎ ሜትሮችን የሚዘልቅ ድንበር ይጋራሉ፡፡
5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ፊንላንድ 13 ሺ ጦር ነው ያላት፡፡ ሆኖም ጦሯን ይበልጥ ለማጠናከርና የተጠባባቂ ጦር ኃይሏን ቁጥር ለማሳደግ እየሰራች ነው፡፡ 900 ሺ ገደማ ተጠባባቂ ኃይል ማሰባሰቧንም፤ ለወታደራዊ ልምምድ የሚመዘገቡ ፈቃደኞች ቁጥር እየጨመረ ነው ያለው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
በፊንላንድ ውትድርና ለወንዶች ግዴታ ነው፡፡ እድሜው የደረሰም ወንድ ሁሉ ይሰለጥንና በተጠባባቂነት ይቀመጣል፡፡
በጦርነት ጊዜ 280,000 ያህል ወታደሮችን ብትመለምል የሚቃጣባትን የትኛውንም ዐይነት ወረራም ሆነ ጥቃት ለመቋቋም እንደምትችልም ፊንላንድ በወታደራዊ ፖሊሲዋ አስቀምጣለች፡፡