የሩሲያው ፕሬዝዳንት የስዊድን እና የፊንላንድ ኔቶን መቀላቀል "ስጋታችን አይደለም" አሉ
ሩሲያ የሀገራቱ አባል መሆን ምላሽ ሊያሰጥ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥታለች
ቱርክ ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባል እንዳይሆኑ ተቃውማለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፒቲን ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ቢቀላቀሉም ለሀገራቸው ስጋት እንደማይሆን አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ከሰሞኑ ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ካሳወቁ በኋላ ነው፡፡
ከሰሞኑ የፊንላንድ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራቸው ኔቶን መቀላቀል እንዳለባት ድጋፍ መስጠታቸውን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሃሳቦች እየተሰነዘሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እስካሁን በፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን የመቀላቀል ሂደት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሩሲያ እና የቱርክ ፕሬዝዳንቶች ናቸው፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ሁለቱ ሀገራት ድርጅቱን መቀላቀላቸው ለሩሲያ ስጋት ባይሆንም ምላሽ ሊያሰጥ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ሰዎች የስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን መቀላቀል አሁን በዩክሬን ያለውን ጦርነት ወደ ሌሎች ሀገራት ሊያዛምተው እንደሚችል እየተነበዩ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ ግን የሩሲያው ፕሬዝዳንት የሀገራቱን ወደ ኔቶ አባልነት የመቅረብ ሂደት በቀጥታ አልተቃወሙም፡፡
ሀገራቱ የኔቶ አባል መሆናቸው ለሞስኮ ስጋት እንደማይሆን ነገር ግን ሂደቱ ግን አጸፋ እንደሚያስፈልገው መናገራቸው ተጨማሪ ጥያቄን የፈጠረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት መነሻ የዩክሬን ኔቶን ለመቀላቀል መወሰኗ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ ደግሞ አሁን ኔቶን መቀላቀል የፈለጉትን ስዊድን እና ፊንላንድን ከሩሲያ ጋር ጦር እንዳያማዝዛቸው ተፈርቷል፡፡
የኔቶ አባል የሆነችው ቱርኩ በፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን በኩል ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን መቀላቀል እንደሌለባቸው አሳውቃለች፡፡
የፊንላንድ ፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን ባሳለፍነው ሳምንት በጋራ ባወጡት መግለጫ ፊንላንድ በአስቸኳይ የኔቶ አባል እንድትሆን መጠየቅ አለባት ብለው ነበር፡፡
ሩሲያ ደግሞ ሀገራቱ ኔቶን የሚቀላቀሉ ከሆነ የኒዩክለር ጦሯን ለማንቀሳቀስ እንደምትገደድ ማስጠንቀቋ ይታወሳል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)አሜሪካ እና ካናዳን ጨምሮ በድምሩ 30 አባል ሀገራት አሉት፡፡ ከዚህ ውስጥ 28ቱ የአውሮፓ ሀገራት ናቸው፡፡
መቀመጫውን ቤልጄም ብራሰልስ ያደረገው ተቋሙ አሁን ላይ 34ኛ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ጀንስ ስቶልተንበርግ እየተመራ ይገኛል።