ሩሲያ፤ ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን የሚቀላቀሉ ከሆነ የኒዩክለር ጦሯን ለማንቀሳቀስ እንደምትገደድ አስጠነቀቀች
ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል አስበዋል ተብሏል
ሩሲያ፤ ሁለቱም ሀገራት ሁኔታዎችን ካልተረዱ ከኑክሌር ጋር ለመኖር መወሰን አለባቸው ብላለች
ሩሲያ፤ ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን እንዳይቀላቀሉ አስጠነቀቀች፡፡
ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን የሚቀላቀሉ ከሆነ ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያንና ሃይፐር ሶኒክ ሚሳኤልን ወደ መሃል አውሮፓ ልታንቀሳቅስ እንደምትችልም ፍንጭና ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች፡፡
ከሩሲያ ጋር 1 ሺ 300 ኪሎ ሜትር የምትዋሰነው ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል እያሰበች ነው ተብሏል፡፡
ከፊንላንድ በተጨማሪ ስዊድንም ተቋሙን ለመቀላቀል ጥረት እያደረገች መሆኗ የተገለጸ ሲሆን ሞስኮ ግን ሁለቱም ከዚህ ጥረታቸው እንዲቆጠቡ እየጠየቀች ነው፡፡
የሩሲያ ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ስዊድንም ፊንላንድም ኔቶን ከተቀላቀሉ ሞስኮ በባልቲክ ባሕር፤ የአየር፣ የባሕርና የምድር ኃይሏን እንደምታጠናክር አስታውቀዋል፡፡
ሜድቬዴቭ ከዚህ በኋላ ከኑክሌር ነጻ የሆነ ባልቲክ በሚለው ጉዳይ ላይ ንግግር ሊኖር እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡
“ሞስክቫ” የተሰኘችው የሩሲያ ግዙፍ የጦር መርከብ በጥቁር ባሕር ላይ ሰመጠች
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት እንዲሁም የአሁኑ የሀገሪቱ ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ከዚህ በኋላ ከኒዩክለር ነጻ ስለሆነ ባልቲክ ንግግር እንደማይኖርና የኃይል ሚዛኑ ወደ መመጣጠን መምጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ሜድቬዴቭ ፊንላንድና ስዊድን ነገሮችን ሊመለከቱ እንደሚችሉ ይህንን ካላደረጉ ደግሞ ``እየቀረባቸው ካለው ኑክሌር ጦር መሳሪያ እና ሃይፐር ሶኒክ ሚሳኤል ጋር አብረው መኖር አለባቸው ማለት ነው`` ብለዋል፡፡
የሩሲያ ቤተ መንግስት (ክሬምሊን) ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፒስኮቭ፤ ሜድቬዴቭ ስለተናገሩት ጉዳይ ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን `` ይህ እኮ በተደጋጋሚ የተባለ ነገር ነው`` ብለዋል፡፡ የኔቶ ወታደራዊ አቅም እየጎለበተ በመሆኑ ፕሬዝዳንት ፑቲን ውሳኔ አሳልፈዋል ብለዋል፡፡