የሞሮኳዊው ታዳጊ ራያን የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ
32 ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ የነበረውን የ5 ዓመቱ ራያንን ለመታደግ ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች መላው ዓለምን ሲያነጋግሩ እንደነበር አይዘነጋም
ራያን ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ እኩለ ሌሊት ነበር ህይወቱ ያለፈው
የሞሮኳዊው ታዳጊ ራያን የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ፡፡
የ5 ዓመቱ ታዳጊ የቀብር ስነ ስርዓት የተፈጸመው ሼፍቹን ተብሎ በሚጠራው ክልል በሚገኘው የትውልድ አካባቢው ነው፡፡
በቀብር ስነ ስርዓቱ የታዳጊውን ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩና ያዘኑ በርካቶች ታድመዋል፡፡
ታዳጊው ራያን የዛሬ ሳምንት ግድም በድንገት ከገባበት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ በቶሎ ለመውጣት ባለመቻሉ ምክንያት ነበር ህይወቱ ያለፈው፡፡
ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ 5 ያህል ቀናትን በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ያሳለፈውን ራያንን በህይወት ለመታደግ የተደረጉ ጥረቶች ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ሌሊቱን ለእሁድ አጥቢያ ራያን ወደነበረበት ጉድጓድ ለመድረስ ቢቻልም ህይወቱን ለማትረፍ ግን አልተቻለም፡፡
ታዳጊው መሞቱንም የሃገሪቱ ንጉሳውያን ቤተሰቦች አስታውቀዋል፡፡
ይህ ወላጆቹን ጨምሮ ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተል የነበረውን የዓለም ህዝብ ያሳዘነ ነው።
ንጉስ መሐመድ ሳድሳዊ (6ኛ)ም ለራያን ወላጆች ደውለው አፅናንተዋል።