ርያንን 5 ቀናትን ካሳለፈበት ጉድጓድ ለመውጣት ቢቻልም በህይወት ለመታደግ ሳይቻል ግን ቀርቷል
ካሳለፍነው ማክሰኞ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ በድንገት በገባበት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ያሳለፈው ሞሮኳዊው ታዳጊ ራያን በህይወት ሳይተርፍ ቀረ።
አምስት ያህል ቀናትን 32 ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ በህይወትና በሞት መካከል ውስጥ ሆኖ ያሳለፈውን የ5 ዓመቱን ታዳጊ በህይወት ለመታደግ የተደረጉ ጥረቶች ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል።
በከፍተኛ የአፈር ቆረጣና ቁፋሮ ርያንን ከቀናት በኋላ ከገባበት ጉድጓድ ለማውጣት ቢቻልም በህይወት ለማትረፍ ግን አልቻለም።
ይህ ወላጆቹን ጨምሮ ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተል የነበረውን የዓለም ህዝብ ያሳዘነ ነው።
የሃገሪቱ ንጉሳዊ ቤተሰብ ርያን ማለፉን በይፋ አስታውቆ ሃዘኑን ገልጿል።
ንጉስ መሐመድ ሳድሳዊ (6ኛ)ም ለርያን ወላጆች ደውለው አፅናንተዋል።
በዚህ የሃዘን ወቅት መላው ሞሮኳዊ እና ሁኔታውን ሲከታተል የነበረ ሁሉ ከጎናቸው ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ታዳጊውን ለማትረፍ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ የድንገተኛ ጊዜ ባለሙያዎችንም አመስግነዋል ንጉስ መሐመድ ሳድሳዊ።
የታዳጊውን ስርዓተ ቀብር ለመፈጸም ሁኔታዎች በመመቻቸት ላይ መሆናቸውንም የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል።