ተጠባቂው የሪያል ማድሪድ እና የማንችስተር ሲቲ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጥጫ ዛሬ ምሽት ይደረጋል
ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት የሁለቱ ቡድን የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ዋንጫውን የማንሳት እድሉ ከፍተኛ ነው

ከ2012/13 የውድድር ዘመን አንስቶ ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው13 ጨዋታዎች አራት ጨዋታዎችን ተሸናንፈዋል
የ15 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በቤርናባው የ2023 ሻምፒዮናውን ማንችስተር ሲቲ ያስተናግዳል፡፡
በሁለቱ ስኬታማ አስልጣኞች ካርሎ አንቾሎቲ እና በፔፕ ጋርድዮላ መካከል የሚደረገው ፉክክር በከፍተኛ ሁኔታ ይጠበቃል፡፡
በስፔን "ዶን ካርሎ" የሚል ቅፅል ስም ያላቸው አንቾሎቲ በአውሮፓ ዋንጫ እና በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ስኬታማው አሰልጣኝ ሲሆኑ ዋንጫውን አምስት ጊዜ በማንሳት ክብረወሰን አስመዝግበዋል፡፡
ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ስድስት የፍጻሜ ውድድር ላይ የደረሱ ብቸኛው አሰልጣኝ ሲሆኑ ልክ እንደ ጋርዲዮላ በ1989 እና 1990 ከኤሲ ሚላን ጋር ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ውድድሩን በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ካሸነፉ ሰባት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ስፔናዊው ፔፕ ጋርዲዮላ በበኩላቸው በባርሴሎና ፣ ባየር ሙኒክ እና ሲቲ ፣ ላሊጋ እና ቡንደስሊጋ ሶስት ጊዜ ዋንጫ ሲያነሱ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ስድስት ዋንጫዎችን አሸንፈዋል።
ኪሊያን ምባፔ ፣ ቪኒሽየስ ጁኒየር፣ ጁዲ ቤሊንግሀም እና ሌሎችም ከሪያል ማድሪድ ጋር፤ ኤርሊንግ ሃላንድ፣ ኬቨን ደብሮይነ እና ፊል ፎደን ደግሞ ከሲቲ ጋር ጥሎ ማለፉን ለመሻገር ይፋጠጣሉ፡፡
ከሁለቱ ቡድኖች ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመኖች የተገናኙባቸውን የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ያሸነፈው ቡድን የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ የማሸነፍ እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
በ2021/22 የውድድር ዘመን የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ሲቲ በአጠቃላይ 6-5 በሆነ ውጤት በሪያል ማድሪድ ተሸንፎ ከዓመት በኋላ የስፔኑን ሀያል ክለብ በድምር ውጤት 5-1 በማሸነፍ የአውሮፓ ሻምፒዮን ለመሆን ችሏል።
ቡድኖቹ ከ2012/13 የውድድር ዘመን ጀምሮ በቻምፒዮንስ ሊግ 13 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች እያንዳንዳቸው 4 ጨዋታዎችን ተሸናንፈው በአምስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ካርሎ አንቾሎቲ በቡድኖቹ መካከል ያለው ፉክክክር ጨዋታቸው ተጠባቂ እንዲሆን እና በደጋፊዎቻቸው መካከልም ውጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም በቅርቡ በተደረገው የባላንዶር የምርጥ ተጫዋቾች ምርጫ ላይ የሻምፒዮንስ ሊጉ አሸናፉ ቡድን አጥቂ ቪኒሽየስ ጁኒየር ሲጠበቅ የሲቲው ሮድሪ ማሸነፉ በቡድኖች መካከል ያለውን የፉክክር አስተያየት ከፍ እንዳደረገው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ዛሬ ምሽት 5:00 ሰዓት በሳንቲያጎ ቤርናባው ላይ የሚደረግ ሲሆን የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ኢቲሀድ ላይ 3 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።