ጃፓናውያን አረጋውያን በእስር ቤቶች ውስጥ መኖርን ለምን መረጡ?
በብቸኝነት የሚንገላቱ አረጋውያን በውጭው አለም ለብቻቸው ከመኖር በእስር ቤቶች ቀሪ ዘመናቸውን ማሳለፍ ምርጫቸው አድርገዋል
ከ 65 ዓመት በላይ ከሆናቸው ሰዎች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በድህነት የሚኖሩ ሲሆን 14.2 በመቶዎቹ ደግሞ የሚያግዛቸው ቤተሰብ ወይም ዘመድ የላቸውም
በጃን የሚገኙ አረጋውያን በሀገሪቱ በሚገኘው የኑሮ ሁኔታ እና በብቸኝነት መስፋፋት ምክንያት በእስር ቤቶች ውስጥ መኖርን እየመረጡ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡
ሲኤንኤን በሀገሪቱ በርካታ አረጋውያን በሚገኙበት የሴቶች እስር ቤት ተገኝቶ በሰራው ዘገባ አረጋውኑ በጡረታ በሚያገኙት ገንዘብ ኑሮን ለመግፋት ከመቸገራቸው ባለፈ ስር የሰደደው ብቸኝነት አረጋውያኑ እስር ቤቶችን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል ብሏል፡፡
የአረጋውያን ህዝብ ቁጥር ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሩ አንድ ሶስተኛ ወይም 36.25 ሚሊየን በሆነባት ሀገር ለብቻቸው የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ሞተው ከወራት በኋላ የሚገኙበት ተደጋጋሚ አጋጣሚ ይከሰታል፡፡
ከቶኪዮ በስተሰሜን በሚገኘው የቶቺጊ የሴቶች እስር ቤት ሴኤንኤን አደረኩት ባለው ጉብኝት በእስር ቤቶች ውስጥ እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ለመቆየት በየወሩ ከ20 – 30 ሺህ የን እንከፍላለን የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ዘግቧል፡፡
አረጋውያኑ በእስር ቤቶቹ ውስጥ ምግብ፣ ነፃ የጤና አገልግሎት እና የአረጋውያን እንክብካቤ ያገኛሉ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በውጭው አለም ያላቸውን ብቸኝነታቸውን የሚያስታግሱበት ጓደኛ በዚህ ያገኛሉ፡፡
አንዳንድ ሰዎች እስር ቤቶች ውስጥ ለመግባት ሆነ ብለው ወንጀለኞችን እንደሚፈጽሙ የጠቀሰው ዘገባው ከጊዜ ወደ ጊዜ በእድሜ የገፉ ታሳሪዎች ቁጥር መጨመሩን አመላክቷል፡፡
ከታሳሪዎቹ መካከል አኪዮ የተባሉት የ81 አመት አዛውንት “በአካባቢየ የኔ የምላቸው ሰዎች ቢኖሩ እና በቂ ገቢ ቢኖረኝ እስር ቤትን አልመርጥም ነበር፤ በየሁለት ወሩ የሚከፈለኝ የጡረታ ገንዘብ ግን የቤት ኪራይ እና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን በቂ ስላልሆነ አሁን ያለሁበትን ህይወት እንድመርጥ አድርጎኛል” ብለዋል፡፡
አኪዮ በመጀመሪያ ወደ እስር ቤት የገቡት በ61 አመታቸው ሲሆን አሁን ላይ በእስር ላይ የሚገኙት ለሁለተኛ ጊዜ በፈጸሙት ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስርቆት በአረጋውያን እስረኞች በተለይም በሴቶች የሚፈጸም የተለመደ ወንጀል ነው።
እ.ኤ.አ. በ 2022 በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 80 በመቶ በላይ የሚሆኑት አረጋውያን ሴት እስረኞች በስርቆት ተጠርጥረው በእስር ላይ እንደሚገኙ የመንግስት መረጃዎች ያመለክታሉ።
በጃፓን ከ 65 ዓመት በላይ ከሆናቸው ሰዎች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በድህነት የሚኖሩ ሲሆን 14.2 በመቶዎቹ ደግሞ የሚንከባከባቸው እና የሚያግዛቸው ቤተሰብ ወይም ዘመድ የላቸውም፡፡
መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ እያደረገ በሚገኘው እንቅስቃሴ በጃፓን የሚገኙ 10 ማዘጋጃ ቤቶች የቅርብ ዘመድ የሌላቸውን አረጋውያን ለመደገፍ የመኖሪያ ቤት ጥቅማ ጥቅሞችን እና ሌሎች እገዛዎችን ለማድረግ የሙከራ ትግበራዎችን ጀምረዋል፡፡