በዓለም ዙሪያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ300,000 በላይ ሲደርስ ከነዚህም 12,944 ሰዎች ሞተዋል
በዓለም ዙሪያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ300,000 በላይ ሲደርስ ከነዚህም 12,944 ሰዎች ሞተዋል
ጣሊያን በ 24 ሰዓታት ውስጥ 800 ገደማ ሞት አስመዘገበች
የጣሊያን የኮሮናቫይረስ ሞት በ 24 ሰዓታት ውስጥ በ793 ጨምሮ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር በሀገሪቱ ወደ 4,825 ከፍ ማለቱን የጣሊያን የዜጎች ጥበቃ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ ቅዳሜ እለት የተመዘገበው የሞት መጠን አርብ ከነበረው በ 20% የሚበልጥ ሲሆን በዓለም ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ወዲህ በአንድ ቀን የተከሰተ ትልቁ የሞት ቁጥር ነው፡፡
በሀገሪቱ የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ለመሆኑ የጤና ባለሙያዎች የተለያዩ ምክኒያቶችን ቢያስቀምጡም ዋናው ግን ከእድሜ መግፋት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ባረጁ ሰዎች ቁጥር ጣሊያን በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ አብዛኛው የቫይረሱ ሟቾችም እድሚያቸው ከ70 ዓመት በላይ ነው፡፡
በጣሊያን በከፍተኛ መጠን በተጎዳው ሎምባርዲ ግዛት 3,095 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል፡፡ በሀገሪቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በ አንድ ቀን በ 6,557 ጨምሮ 53,578 ደርሷል፡፡
በአፍሪካ 41 ሀገራት እና 2 ግዛቶች ኮሮና ቫይረስ ተዳርሶባቸዋል
ሀገራት (41) እና ግዛቶች (2) በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር (1117)፡- አልጄሪያ (102) ፣ አንጎላ (2) ፣ ቤኒን (2) ፣ ቡርኪና ፋሶ (64) ፣ ካሜሩን (27) ፣ ኬፕ ቨርዴ (1) ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ (3) ፣ ቻድ (1) ፣ ኮንጎ (1) ፣ ኮትዲቮር (14) ፣ ጅቡቲ (1) ፣ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ (18) ፣ ግብፅ (285) ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ (4) ፣ እስዋቲኒ (1) ፣ ኢትዮጵያ (11) ፣ ጋቦን (4) ፣ ጋምቢያ (1) ፣ ጋና (19) ፣ ጊኒ (2) ፣ ኬንያ (7) ፣ ላይቤሪያ (3) ፣ ማዳጋስካር (3) ፣ ሞሪሺየስ (14) ፣ ሞሪታኒያ (2) ፣ ሞሮኮ (86) ፣ ናሚቢያ (3) ፣ ኒጀር (1) ፣ ናይጄሪያ (22) ፣ ሩዋንዳ (17) ፣ ሴኔጋል (47) ፣ ሲሸልስ (7) ፣ ሶማሊያ (1) ፣ ደቡብ አፍሪካ (240) ፣ ሱዳን (2) ፣ ታንዛኒያ (6) ፣ ቶጎ (9) ፣ ቱኒዚያ (60) ፣ ዛምቢያ (2) ፣ ዚምባብዌ (2) ፣ ኤርትራ (1)። ግዛቶች (2)፡- ከጉዳዮች ጋር-ማዮት (4) ፣ ሪዩኒየን (15)
ሞት ያስተናገዱ ሀገራት (9) ፣ አጠቃላይ ሞት (28)፡- አልጄሪያ (9) ፣ ቡርኪና ፋሶ (3) ፣ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ (1) ፣ ግብፅ (8) ፣ ጋቦን (1) ፣ ሞሪሺየስ (1) ፣ ሞሮኮ (3) ፣ ሱዳን (1) ፣ ቱኒዚያ (1)
ያገገሙ ታማሚዎች ያሉባቸው ሀገራት (10) ፣ ያገገሙት ብዛት (103):- አልጄሪያ (32) ፣ ቡርኪና ፋሶ (4) ፣ ካሜሩን (2) ፣ ግብጽ (39) ፣ ኢትዮጵያ (4) ፣ ሞሮኮ (2) ፣ ናይጄሪያ (2) ፣ ሴኔጋል (5) ፣ ደቡብ አፍሪካ (12) ፣ ቱኒዚያ (1)
ማሩዋን ፌላኒ፣ ዲባላ እና ማልዲኒ በኮሮና ቫይረስ ተያዙ
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድና ኤቨርተን ተጫዋች ማሩዋነም ፌላኒ ባደረገው ምርመራ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘበት ተገለጸ፡፡ በሻንዶንግ ሉኔንግ ታይሻን ክለብ የሚጫወተው ፌላኒ በቫይረሱ እንደተያዘ በትዊተር ገጹ አስፍሯል፡፡ ተጫዋቹ አሁን ላይ በሆስፒታል የህክምና ክትትል እያደረገ ነው፡፡
ከፌላኒ በተጨማሪ የጁቬንቱስና የአርጀንቲና የፊት መስመር ተጫዋች ፓውሎ ዲባላ፣ የቀድሞው የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን አምበል ፓውሎ ማልዲኒና ልጁ ዳኒኤል ማልዲኒ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሏል፡፡
የቻይና ፕሬዚዳንት በአውሮፓ ኮሮና በከፍተኛ ሁኔታ ከተስፋፋባቸው ሃገራት መሪዎች ጋር ተወያዩ
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ባለባቸው ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ስፔንና ሰርቢያ መሪዎች ጋር መወያየታቸው ተሰማ፡፡ ፕሬዚዳንቱ አሁን ላይ ያለውን ዓለም አቀፍ ችግር አስመልክቶ አጋርነታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኤል ማክሮን ጋረ የተወያዩት የቻይናው ፕሬዚዳንት ቻይና በከፍተኛ ደረጃ ችግር ላይ በነበረችበት ጊዜ ፈረንሳይ አድርጋው ለነበረው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በዓለም ደረጃ ችግር የሆነውን የኮሮና ቫረስን እርስ በእርሳችን ተባብረን እናሸንፋለን ያሉት የቻይናው ፕሬዚዳንት ለፈረንሳይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር ባደረጉት ውይይትም ቻይና ለጀርመን አስፈላጊውን ድጋፍ ታድርጋለች ብለዋል፡፡
ሺ ከስፔኑ ንጉስ ፌሊፕ 6ኛ ጋር ባደረጉት ውይይት የሰው ልጆች በጋራ ብዙ ነገር መስራት ስለሚችሉ በችግር ጊዜም ትብብር አሸናፊ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ቻይናና ስፔን ይህንን ወረርሽኝ ለማሸነፍ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ቻይና ለሰርቢያ የቫይረሱን መከላከያ ቁሳቁሶችና የህክምና መሳሪዎችን ጭምር የላከች መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ሀገሪቱ ወደ ሰርቢያ የላከቻቸው የህክምና ቡድን አባላት ቤልግራድ ሲደርሱ የሰርቢያው ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ቩሲች ተቀብለዋቸዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በደስታ ብዛት የቻይናን ሰንደቅ ዓላማ መሳማቸውንም ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የተጠቂዎች ቁጥር በፍጥነት እያሻቀበ ነው
በዓለም ዙሪያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ300,000 በላይ ደርሷል፡፡ ከነዚህም 12,944 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡
ቻይና፣ ጣሊያን፣ ኢራን፣ ስፔን፣ ጀርመን፣ ዩኤስ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም በከፍተኛ መጠን የተጠቁ እና አብዛኛው ታማሚዎች የሚገኙባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
የቫይረሱ ስርጭት አሁንም ከቻይና ውጭ በፍጥነት እየተዛመተ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሀገራት ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚወስዷቸውን እርምጃዎች አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ቻይና ለአራተኛ ተከታታይ ቀኝ በሀገሯ የቫይረሱን ተጠቂ አላገኘችም፡፡ ይሁን እንጂ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ማንኛውም ዓለማቀፍ በረራ መዳረሻውን ከቤጂንግ ውጭ በሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲያደርግ ሀገሪቱ ወስናለች፡፡
የተለያዩ ምንጮችን ለዘገባው በምንጭነት ተጠቅመናል