በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ በተመድ ተመረጠ
በስፔኗ ዋና ከተማ ትናንት የተጀመረው 24ኛው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጉባኤ ለሦስት ቀናት ይቆያል
የቱሪዝም ሚኒስቴር ወንጭ ሐይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ የተመረጠው የአካባቢው ነዋሪዎች አካባቢውን በመንከባከባቸው ነው ብሏል
በስፔን ማድሪድ እየተካሄደ ባለው በ24 ኛው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጡ ተገለጸ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ከ170 የቱሪዝም መንደሮች መካከል ቀዳሚ ሆኖ መመረጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የቱሪዝም ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡ የወንጪ ሃይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ የተመረጠው ባለው የተለየና ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት መሆኑም ተገልጿል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች አካላት ወንጪ ሐይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ ለመመረጥ እንዲበቃ የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ በመንከባከባቸውም ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
የወንጪ ሐይቅ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ማግኘቱ ለሌሎችም አረዓያ የሚሆንና የበለጠ ለመሥራት እንደሚያነሳሳም ሚኒስትሯ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ በስፔኗ ዋና ከተማ ትናንት የተጀመረው 24ኛው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጉባኤ ለሦስት ቀናት ይቆያል።
ጉባዔው በተለይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ዘርፍ ችግሮችን በተመለከተ ውይይት ያደርጋል ተብሏል፡፡
የወንጪ ሐይቅ “በገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ከተካተቱት መካከል አንዱ ሲሆን፤ የወንጪ-ደንዲ ኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት መጀመሩም ይተወሳል፡፡ በአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ይህ ፕሮጀክት በአከባቢው የላቀ የጎብኚዎች መስዕብን እምርታ ሊያሳድግ እንደሚችል ተገልጿል፡፡