የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንገ ዪ ከአሜሪካው አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ጋር ተወያይተዋል
ቻይና አሜሪካ ቀይ መስመሮቿን እንዳታልፍ አስጠንቅቃለች።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንገ ዪ በቤጂንግ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የአሜሪካው አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ነው አሜሪካ የቻይናን ቀይ መስመሮች እዳትጥስ ያስጠነቀቁት ተብሏል።
ዋንገ ዪ በውይይታቸው ወቅት የቻይና ቀይ መስመሮች ያሏቸውንም ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ ቀይ መስመሮቹም “ሉዓላዊነቷ፣ ደህንነቷ እና ልማትቷ መሆኑን አስታውቀዋል።
ንግግራውን ማስጠንቀቂያ በሚመስልና በጥያቄ የጀመሩት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንገ ዪ፤ “ቻይና እና አሜሪካ በተረጋጋ ሁኔታ ወደፊት ለመራመድ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይከተላሉ ወይንስ ወደ የቁልቁለት ሽክርክሪት ይመለሱ?” ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንገ ዪ አክለውም፤ የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት መረጋጋት ቢጀምርም አሁንም "በአሉታዊ ጉዳዮች" እየተፈተነ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በቻይና አሜሪካ ግንኙነት ውስጥ "በአሉታዊ ጉዳዮች" አሁንም እየጨመሩ መጥተዋል ያሉት ዋንግ ዪ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የማሳደግ ሂደትም “ሁሉም አይነት ችግሮች እያጋጠመው ነው" ብለዋል።
ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ቻይናን የጎበኙት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ ለቻይናው አቻቸው ዋንግ ዪ የሰጡት አስተያየት የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር።
አንቶኒ ብሊንከን በንግግራቸውም “ቤጂንግ እና ዋሽንግተን ግንኙነታቸውን “በነቃ ዲፕሎማሲ” ለማራመድ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
አሜሪካ እና ቻይና በታይዋን ጉዳይ በተደጋጋሚ ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸውም ይታወቃል።
ቻይና ከዚህ ቀደም አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ቀይ መስመር እንዳታልፍ ስትል በተደጋሚ ስታሥጠነቀቅ መቆየቷም ይታወሳል።