የቀይ ባህር ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ቶሎ ካልተጠገነ ዓለምን 20 ቢሊየን ዶላር ያከስራል ተባለ
ማስተላለፊያ መስመሩን ለመጠገን ሀገራት ገንዘብ እንዲያዋጡ ተመድ አሳስቧል
ሳዑዲ አረቢያ 10 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች
የቀይ ባህር ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ቶሎ ካልተጠገነ ዓለምን 20 ቢሊየን ዶላር ሊያሳጣ አንደሚችል ተመድ አስታወቀ።
በቀይ ባህር ላይ ያለው የዓለም ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር የህልውና አደጋ እንደተደቀነበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ገልጿል።
ከ45 ዓመት በፊት በቀይ ባህር ላይ የተገነባው የዓለም ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር እድሳት ካልተደረገለት ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ወደ ቀይ ባህር ዉሃ ገብቶ አካባቢውን ሊበከል እንደሚችልም ተመድ አስጠንቅቋል።
ጥገናው በፍጥነት ሳይከናወን ከቀረ እና ቀይ ባህር እና አካባቢው በነዳጅ ከተበከለ በአሳ እርባታ እና ሌሎች ስራዎች የተሰማሩ የአካባቢው ሀገራት ዜጎች ችግር ውስጥ እንደሚገቡም ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ ታንከር ጥገናው ከዚህ በፊት መከናወን ያለበት ቢሆንም በየመን ባለው የእርስር በርስ ጦርነት ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።
የ150 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለከፋ አደጋ መጋለጡን የገለጸው ድርጅቱ ሀገራት በአፋጣኝ ገንዘብ አዋጥተው እንዲጠግኑት አሳስቧል።
የተመድን ማሳሰቢያ ተከትሎም ሳውዲ አረቢያ 10 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን አስታውቃለች።
የቀይ ባህር ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ከ1 ሚሊየን በላይ በርሜል ነዳጅ ወደ ተለያዩ የዓለማችን ሀገራት የማሰራጨት አቅም ዓለው።
ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ በወቅቱ ካልተጠገነ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የ20 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ያደርሳል ያለው ተመድ ጉዳቱን ማስቀረት ካልተቻለ በዓለም ላይ ከባድ የስነ ምህዳር ቀውስንም ያስከትላል ሲል አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀይ ባህር ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመርን ለመጠገን ከሚያስፈልገው 80 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ባሳለፍነው ሳምንት ባካሄደው የገቢ ማስገኛ ፕሮግራም ላይ 33 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ገልጿል።