ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገባችበት ጦርነት የዓለም ነዳጅ ዋጋን በማናር ላይ ይገኛል
ሩሲያ በታሪክ ከፍተኛውን ገቢ ከነዳጅ እንደምታገኝ ገለጸች።
የሩሲያ ፋይናንስ ሚኒስትር እንዳሉት በተያዘው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ተጨማሪ 14 ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ እንደምታገኝ ይጠበቃል።
ሚኒስትሩ አንተን ሲሉአኖቭ እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት ሩሲያ ከነዳጅ ገበያ ያገኘችው ዓመታዊ ገቢ 9 ቢሊየን ዶላር ነበር።
በተያዘው ዓመት ተጨማሪ 14 ቢሊየን ዶላር ነዳጅ እንደምታገኝ የገለጸችው ሩሲያ፤ ገቢውን የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት እንደምታውለውም ሚኒስትሩ አክለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከዩክሬን ጋር ለጀመረችው ጦርነት ወጪ እንደምታውለውም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ሶስት ወራት አልፎታል።
ጦርነቱን ተከትሎም በአሜሪካ አስተባባሪነት ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦችን የተለያዩ ሀገራት በሩሲያ ላይ ጥለዋል።
ሩሲያም ወዳጅ አይደሉም ያለቻቸውን ሀገራት ነዳጇን በሩብል እንዲከፍሉ ትዕዛዝ ማስተላለፏን ተከትሎ የአውሮፓ ኩባንያዎች ነዳጅ በሩብል መግዛት ጀምረዋል።
40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ ፍላጎት የምታሟላው ሩሲያ ነዳጇን እንዳትሸጥ ማዕቀብ ቢጣልባትም ሀገራት ግን ምርጫ አጥተው አሁንም የሩሲያን ነዳጅ በመግዛት ላይ ናቸው።
በዚህ ጦርነት ምክንያት የዩክሬን ዋና ዋና የሚባሉ ከተሞችን ጨምሮ የንግድ ማሳለጫ ወደቦች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።