ደቡብ ሱዳን የሳቫና ሪፐብሊክ የናይል ሪፐብሊክ እና የኩሽ ግዛት እንድትባል ሃሳብ ቀርቦ ነበር
የደቡብ ሱዳኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ሀገራቸው ስያሜዋ እንዲቀየር ሃሳብ ማቅረባቸውን አስታወቁ፡፡
የተቃዋሚ መሪ የሆኑት እና አሁን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው እያገለገሉ ያሉት ማቻር ደቡብ ሱዳን የሚለው ስያሜ መልክ ዓምድራዊ አቅጣጫን እንጅ ገለልተኛ የፖለቲካ ስያሜን እንደማያመለክት ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ብቻ የሀገሪቱን ስም መሆን ያለበት ደቡብ ሱዳን ሳይሆን የሱዳን ሕዝቦች ሪፐብሊክ መሆን አለበት ብለዋል ሪክ ማቻር፡፡
ማቻር ዛሬ በሀገሪቱ ዋና ከተማዋ ጁባ በፓርቲያቸው ዋና ጽህፈት ቤት ባደረጉት ንግግር ከ10 ዓመት በፊት ከሱዳን ነጻነቷን የተቀዳጀችው ደቡብ ሱዳን ተገቢውን ስያሜ እንዲታገኝ አሁንም በሀገሪቱ መሪዎች እና በሕዝብ መካከል ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማቻር አክለውም “ለሀገራችንን የሚመጥን ስያሜ በመምረጥ ሂደት ላይ ተጨማሪ ውይይቶችን እናደርጋለን” ያሉ ሲሆን አሁን ያለው ስያሜ “የትግላችንን ታሪካዊ ጥልቀት ያሳጣዋል” ብለዋል፡፡
በፈረንጆቹ ሃምሌ 2011 ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ስታውጅ ፓርላማው ባደረገው ውይይት ስያሜዋ ደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ምንም እንኳ የሀገሪቷ ስያሜ ደቡብ ሱዳን ይሁን እንጅ አሁንም በስያሜው ላይ በሀገሪቱ ምሁራን መካከል ክርክር እንዳለ ይገለጻል፡፡
በርካታ ፖለቲከኞች እና ጸሃፊዎች ሀገሪቱን የሳቫና ሪፐብሊክ፤ የናይል ሪፐብሊክ እና የኩሽ ግዛት እንድትባል አዳዲስ ሀሳቦችን ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡