የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ "የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው የኃይል እርምጃ" ማዘኑን ገለጸ
አዲስ በተቋቋመው የሸገር ከተማ መስጅዶች እየፈረሱ ነው በሚል ነበር ባለፈው አርብ እለት ተቃውሞው የተደመረው
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ምክር ቤቱ የጀመረው ውይይት እስኪጠናቀቅ ህዝበ ሙስሊሙ በትእግስት እንጠብቅ ጠይቋል
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አባባ አኑዋር መስጅድ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ "የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ ጉዳት መድረሱ" እንዳሳዘነው ገልጿል
ጉባዔው ባለፈው አርብ አኑዋር መስጅድ እና በኑር መስጅድ በተነሳው ተቃውሞ ወቅት ባልተመጣጠነ የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን በርካቶች መቁሰላቸውን አስታውሷል።
የአዲስ አበባ ፖሊስም በወቅቱ በሰጠው መግለጫ በተፈጠረው ችግር የሰው ህይወት ማለፉን እና በጸጥታ ኃይሎችም ላይ ጉዳት መድረሱን መግለጹ ይታወሳል።
አዲስ በተቋቋመው የሸገር ከተማ መስጅዶች እየፈረሱ ነው በሚል ነበር ባለፈው አርብ እለት ተቃውሞው የተደመረው።
ይህ ተቃውሞ ለሁለተኛ ጁመዓ የቀጠለ ሲሆን በዛሬው እለትም ከሶላት በኋላ በተፈጠረ ችግር በምእመናን ላይ ጉዳት መድረሱን እማኞች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
እንደ እማኞቹ ገለጻ ከሆነ ከፖሊስ በተኮሰ ጥይት ተመተው የወደቁ እና ህይወታቸው ያለፈም እንዳሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአይን እማኝ ገልጸዋል።
ባለፈው አርብ የተከተውን ችግር ተከትሎ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ችግሩን ለመፍታት ከመንግስት ጋር እንደሚነጋገር አሳውቆ ነበር።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ምክር ቤቱ የጀመረው ውይይት እስኪጠናቀቅ ህዝበ ሙስሊሙ በትእግስት እንጠብቅ ጠይቋል።