በጦርነት የተፈናቀሉ የትግራይ ነዋሪዎችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው መመለስ መጀመራውን ተከትሎ በአካባቢው ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ወደ ጠ(ጸ)ለምት ወረዳዎች ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራው በተንኮል የታጀበ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል
ወደ ቀድሞ ቤታችን ተመልሰናል ያሉ ተፈናቃዮች በበኩላቸው ንብረታቸው ተዘርፎ እንደጠበቃቸው እና አሁንም የደህንት ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ በትግራይ ታጣቂዎች መመታቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ይህ ጦርነት ከሁለት ዓመት በኋላ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ጦርነቱ ቆሟል፡፡
የዚህ ስምምነት አንድ አካል የሆነው በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው የመመለስ ስራው በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ከሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮም የአማራ እና ትግራይ ክልል ይገባኛል ጥያቄ ከሚያነሱባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ወደ ሆነው የአማራ ክልል ጠለምት የትግራይ ክልል ደግሞ ጸለምት በሚል በሚጠራቸው ወረዳዎች ተፈናቃዮችን መመለስ ተጀምሯል፡፡
አል-ዐይን አማርኛ በነዚህ እና አጎራባች አካባቢዎች ተፈናቃዮችን የመመለሱ ሂደት ምን ይመስላል? ሲል ነዋሪዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡
በጠ(ጸ)ለምት አካባቢ የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሱባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በሆነው ማይጠ(ጸ)ብሪ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ እንዳሉን ከሆነ ለደህንነታቸው ሰግተው የፈተናቀሉ ንጹህ እና እውነተኛ ተፈናቃዮች መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት እኝህ አስተያየት ሰጪ ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቤታቸው መግባታቸውን በዚህም ህዝቡ ተቃውሞ እንደሌለውም አክለዋል፡፡
ይሁንና በተፈናቃዮች ሰበብ ታጣቂዎች፣ የቀድሞ የህወሃት አመራሮች እና ሌሎች ሰዎች ከነ ጦር መሳሪያቸው ወደ ጠ(ጸ)ለምት ወረዳዎች ገብተዋል ብለዋል፡፡
በአንድ ተፈናቃይ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከ17 እስከ 30 የታጠቁ ሰዎች መታወቂያ እየተሰጣቸው ገብተው እየኖሩ ነው ያሉን እኝህ አስተያየት ሰጪ በትግራይ እና አማራ ክልል የሚነሱ ቅሬታዎችን እንዲሰሙ በሚል ሃላፊነት ለተሰጣቸው ሰዎች አሳውቀናል ነገር ግን እስካሁን የተወሰደ መፍትሔም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
የተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቤታቸው መግባታቸውን እና ተያያዥ ስራዎችን እንዲሰሩ ከአማራ እና ትግራይ ክልል የተወከሉ አመራሮች በትግራይ በኩል ያሉት የቀድሞ አመራሮች መሆናቸውን እና የፖለቲካ ስራ የሚሰሩ ናቸው ያሉት እኝህ አስተያየት ሰጪ በአማራ ክልል በኩል ግን የተወከሉት አካባቢውን በሚገባ የማያውቁ ችግሮች ሲፈጠሩም ማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ የማያደርጉ በመሆናቸው ይህ እንዲስተካከልልን አካባቢውን እያስተዳደረ ላለው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ብናመለክትም መፍትሄ አልተሰጠም ሲሉም አክለዋል፡፡
በማይጠ(ጸ)ብሪ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆነ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበኩሉ ከተፈናቃዮቹ ጋር ተዳብለው እንዲገቡ እና እንዲኖሩ የተደረጉ የትግራይ ታጣቂዎች ምሽቶችን ከለላ በማድረግ ሰዎችን እያሸማቀቁ፣ ቤት እየሰበሩ እየገቡ ሰዎችን እንደሚደበድቡ እና ተጽዕኖ ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በአካባቢዎቹ በቅርቡ ጊዜያዊ አስተዳድር ይዋቀራል መበሉን ተከትሎ ከተፈናቃዮቹ ጋር ተዳብለው እንዲኖሩ የተደረጉት ታጣቂዎች በአመራር ቦታዎች ላይ ብልጫ እንዲያዝ ለማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው እየሰሩ መሆኑን እናውቃለን ያሉት እኝህ አስተያየት ሰጪ እየተደረገ ያለው ነገር ሁሉ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያለመ አይመስልም ዘላቂ ሰላምም የሚያመጣ አይሆንም ሲሉም ስጋታቸውን አክለዋል፡፡
ከአራት ቀናት በፊት ወደ ቀድሞ መኖሪያ መመለሱን የነገረን መምህር ጉኡሽ ደሳለኝ በበኩሉ በማይጸ(ጠ)ብሪ ከተማ ተወልዶ ማደጉን እና በዚሁ ከተማ ባለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲያስተምር እንደነበር ገልጾ ከዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ ቤቱ በመመለሱ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ይሁንና ከእሱ በፊትም ሆነ አሁን ላይ እየገቡ ላሉ ተፈናቃዮች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን እርዳታ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ እሱን ጨምሮ ሌሎችም ተፈናቃዮች በችግር ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
ከእርዳታ ባለፈም በከተማዋ ታጣቂዎች አሁንም ትጥቃቸውን እንዳልፈቱ፣ ከጦርነቱ በኋላ ተመስርተው የነበሩ አስተዳድሮች አሁንም እንዳልፈረሱ ይህም ለተፈናቃዮች ስጋት መደቀናቸውን አክሏል፡፡
በተለይም የአማራ ክልል ታጣቂዎች እና አሁን ከተፈናቃዮች ጋር የገቡት ታጣቂዎች ወደ ጸ(ጠ)ለምት ከተማ በመግባታቸው በአካባቢው የጸጥታ ስጋት መደቀኑንም መምህር ጉኡሽ ጠቅሷል፡፡
በአካባቢው ሸቀጦችን እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች እጥረት እንዳለ የገለጸው ይህ አስተያየት ሰጪ ከማይጸ(ጠ)ብሪ ሽሬ የሚያስኬደው መንገድ እስካሁን እንዳልተከፈተም ተገልጿል፡፡
ላለፉት ሶስት ዓመታት በእንዳባጉና ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተጠልሎ ከስድስት ቀናት በፊት ወደ ማይጸ(ጠ)ብሪ ከተማ መመለሱን የነገረን ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በጦርነቱ ከተፈናቀሉ ሰዎች ጋር ከ2013 ዓ.ም በፊት ታጣቂዎች የነበሩ ሰዎችም አብረዋቸው መመለሳቸውን ጠቅሷል፡፡
በትግራይ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በዋሉ የራያ እና አላማጣ አካባቢዎች ህይወት ምን ይመስላል?
ይሁንና ከጦርነቱ በኋላ በማይጸ(ጠ)ብሪ እና አጎራባች የገጠር ቀበሌዎች የመጡ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ አለመደረጉ እና ተቋቁሞ የነበረው አስተዳድር አለመፍረሱ አሁንም በአካባቢው ተጨማሪ ግጭት እንዲከሰት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ስጋቱን አጋርቷል፡፡
ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ከጸ(ጠ)ገዴ ወረዳ ሀድነት ቀበሌ የተፈናቀለው በበኩሉ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በጦርነቱ ምክንያት ከሚወደው እርሻ ስራው ተፈናቅሎ ህይወቱን በመከራ እየመራ መሆኑን ነግሮናል፡፡
ተፈናቃዮችን መመለስ መጀመሩ ሲጠብቀው እንደነበር የተናገረው ይህ አስተያየት ሰጪ እስካሁን ከወልቃይት እና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎችን መመለስ እስከሚጀምር በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን አክሏል፡፡
በተፈናቃዮች ስም የሚሰሩ የፖለቲካ ስራዎች ለአብነትም ታጣቂዎችን እና የፖለቲካ አመራሮችን በተፈናቃዮች ስም የማስገባት ሙከራዎች መኖራቸው ወደ ቀድሞ እርሻው እንዳይመለስ ሊያደርጉት እንደሚችሉም ይህ አስተያየት ሰጪ ስጋቱን ተናግሯል፡፡
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዜዳንት ሌ/ ጀነራል ታደሰ ወረደ ከሰሞኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው የመመለሱ ስራው ይቀጥላል፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ተፈናቃዮችን የመመለሱ ስራውን እናጠናቅቃለን በሚል የተያዘው እቅድ ያልተሳካው በአማራ ክልል በኩል ተገቢው ስራ ባለመሰራቱ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የራያ እና ጸለምት አካባቢ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቤታቸው የመመለስ ስራው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ ወደ ቀሪ አካባቢዎችም ተፈናቃዮችን መመለስ እንጀምራለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የወልቃይት ሰቲት ሁመራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አመራር የሆኑት አታላይ ዛፌ በበኩላቸው ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው መመለስ በሚል ስም የህወሃትን አስተዳድር አናቋቁምም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ራያ እና ጠለምት እየተሰራ ያለው ህወሃትን መመለስ እንጂ ተፋናቃዮችን መመለስ አይደለም” ያሉት አቶ አታላይ በወልቃይት ሰቲት ሁመራ አካባቢዎች ይህን ስህተት አንደግምም ብለዋል፡፡
አቶ አታላይ አክለውም “ጦርነቱ እንደተጀመረ ተደናግጠው እና ለደህንነታቸው ፈርተው የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን እነዚህ ሰዎች ወደ ቤታቸው መመለስ አለባቸው፣ ነገር ግን ሆን ብለው ንጹሃንን በማንነታቸው ሲገድሉ የነበሩ ፖለቲከኞች ግን በተፈናቃዮች ስም እንዲገቡ እና ዳግመኛ እንዲገድሉ የሚፈቅድ ህዝብ አይኖርም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡