በትግራይ ክልል ከነበሩት 6378 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ወደ ስራ የገቡት 227 ብቻ መሆናቸውን ክልሉ ገለጸ
በጦርነቱ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሰራ አልገቡም ብሏል ክልሉ
ባንኮች ወደ ስራ የገቡትን እንዱስትሪዎች ስራ ያልሰሩባቸውን የጦርነት አመታት ጭምር የብድር ወለድ እንዲከፍሉ እየጠየቋቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከ2013 ጥቅምት ወር ጀምሮ የተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ ማህበራዊ፣ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራን አድርሷል፡፡
በፌደራል መንግስቱ እና በህውኃት መካከል በትግራይ ሲደረግ የነበረው ጦርነት እየተስፋፋ መጥቶ አጎራባች የአፋር እና አማራ ክልሎች ላይም ተዛምቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በጦርነቱ የደረሰው አጠቃላይ ውድመት እና ኪሳራ ምን ያህል እንደሆነ በመንግስት በኩል ይፋ የሆነ አሀዝ የለም።
የትግራይ ክልል በዚህ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ክልሉ ከጦርነቱ በፊት በርካታ ከፍተኛ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መገኛ እንደነበርም ይታወቃል፡፡
የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር ዳዊት ገብረጻዲቅ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ከጦርነቱ በፊት በክልሉ 6378 ኢንዱስትሪዎች እንደነበሩ ይናገራሉ። ነገርግን አቶ ዳዊት እንደገለጹት ከነዚህ ውስጥ አሁን ወደ ስራ የገቡት 227 ብቻ ናቸው።
ዳይሬክተሩ በክልሉ ቁጥጥር ስር በሚገኙ 57 ወረዳዎች ወደ ስራ ተመልሳዋል ከተባሉ 227 ኢንዱስትሪዎች መካከል 200 አነስተኛ፣ 15 መካከለኛ እና 12 ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት የሚያቀርቡት ሁለት ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን የሚያመርቱ፣ ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች የሚቀርቡ ግብአቶችን በማቅረብ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ የነበራቸው ናቸው ብለዋል አቶ ዳዊት፡፡
ከዚህ ባለፈም ከፍተኛ ፋብሪካዎችን ሳይጨምር በመካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ቁጥራቸው ከ10ሺ የሚልቁ ዜጎች ተቀጥረው ይሰሩ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የኢንዱስትሪ ሰራተኛ እና ባለሙያ ተበታትኖ ያገኛል ያሉት አቶ ዳዊት በህይወት የሚገኙ ሰራተኞችን ወደ ስራ ገበታቸው ለመመለስ አዳዲሶችንም ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በፋብሪካዎች ላይ የደረሰው አጠቃላይ የጉዳት መጠን ምን ያህል ነው ብለን የጠየቅናቸው ዳይሬክተሩ፤ሙሉ ለሙሉ ጉዳት የደረሰባቸው እና ወደ ስራ የማይመለሱ፣ በከፊል የወደሙ እና ጥቂት ጉዳት ያስተናገገዱ ሲሉ ከፍለዋቸዋል፤ የደረሰባቸውን የገንዘብ ኪሳራ በተመለከተ ገና ጥናት በመከናወን ላይ በመሆኑ በቁጥር ማስቀመጥ አይቻልም ነው ያሉት፡፡
የወደሙ ፋብሪካዎችን ስራ ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት ከፌደራል መንግስት የሚደረገው ድጋፍ በቂ የሚባል አይደለም ያለው ቢሮው ተነቅለው የተወሰዱ እና ውድመት የደረሰባቸውን ማሽነሪዎች ለመተካት የውጭ ምንዛሬ እና የበጀት እጥረት ፈተና ሆኖብኛል ብሏል፡፡
አቶ ዳዊት ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚኖረውን የፋይናንስ ጫና ለማርገብ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ብድሮችን፣ የቀድሞ ብድሮችን የመክፈያ ጊዜ ማራዘምን እና የውጭ ምንዛሪ ማኔጅመንት እርምጃዎችን ጨምሮ - የፋይናንስ እገዛ ላይ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳዊት አክለውም ባንኮች ኢንዱስትሪዎች ስራ ያልሰሩባቸውን የጦርነት አመታት ጭምር የብድር ወለድ ኢንዲከፍሉ እየጠየቁ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ ካሳለፈው የግጭት ግዜ አንጻር ፋብሪካዎቹም ከሚያንቀሳቅሱት የሰው ሀይል እና ኢኮኖሚ አኳያ በፋይናንስ እና በውጭ ምንዛሬ ዙርያ ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል
የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም ባንክ እና በልማት አጋሮች የቴክኒክ ድጋፍ በመታገዝ የትግራይ ክልሉን ጨምሮ በሀገሪቱ ግጭቶች ያደረሷቸውን ውድመቶችና ጥፋቶች እንዲሁም የፈጠሯቸውን ፍላጎቶች በተመለከተ አካታች መረጃ ለመስጠት፣ የጉዳትና የፍላጎት ግምገማ ወይም Damage and Needs Assessment (DaNA) ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የጉዳትና የፍላጎት ዳሰሳ ግምገማው ከፌደራል እና ከክልል የመንግስት ተቋማት፣ ከልማት አጋር ድርጅቶች፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ አካላት፣ እና ከግሉ ዘርፍ ግጭቶች በተከሰተባቸው ቦታዎች ላይ በመገኘትም ሆነ በርቀት በተገኙ መረጃዎች ላይ የተደረጉ ትንታኔዎችን መሠረት በማድረግ ግጭቶቹ ከኅዳር 2013 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም ያደረሷቸውን ጉዳቶች ይተነትናል።
ግምገማው በአፋር፣አማራ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ትግራይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ (በትላልቅ እና መካከለኛ ደረጃ አምራቾች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ አንተርፕራይዞች እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት አጠቃላይ ጉዳት መድረሱን አስቀምጧል፡፡
በህውኃት እና በፌደራል መንግስት መካከል ባለፈው አመት ህዳር በፕሪቶርያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሰሜኑ ጦርነት መቋጫ ማግኝቱ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ሁለቱን ወገኖች ሲያደራድሩ ከነበሩ አካላት መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ሴማፎር በተባለ አንድ ድረ-ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ በሰሜን ኢትዮጵያ መልሶ ግንባታ ለማከናወን 25 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል።