በአፍሪካ 67 ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት መታሰራቸውን የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ አስታወቀ
ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ጋዜጠኞችን በማሰር ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
የአፍሪካ ሀገራት የሳይበር ፣ የጸረ ሽብር እና የብሔራዊ ደህንነት ወንጀል ህጎችን ጋዜጠኞችን ለማሳር እያዋሉት ነው ተብሏል
በመላው አፍሪካ 67 ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት ብቻ መታሰራቸውን አለም አቀፉ የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ (ሲፒጄ) ሪፖርት አመላከተ፡፡
የተመዘገበው እስር በአህጉሪቷ በነጻ ሀሳብን የመግለጽ መብት ፣ የመረጃ ነጻነት እና ሌሎችም መብቶች እያሽቆለቆሉ እንደሚገኙ ማሳያ ነው ብሏል ሪፖርቱ ፡፡
ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ሲፒጄ እስከ ታህሳስ 1 ድረስ በአለም አቀፍ ደረጃ 361 ጋዜጠኞች መታሰራቸውን የገለጸ ሲሆን በአፍሪካ የተመዘገበው ዕስር እስከዛሬ ከነበሩት በመጠኑ ሁለተኛው ነው ተብሏል
በሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ “መንግስታት በጋዜጠኞች ላይ የብሔራዊ ደህንነት፣ የፀረ-ሽብርተኝነት እና የሳይበር ወንጀል ህጎችን በመሳሪያነት በመጠቀም ጋዜጠኞችን ለማሳደድ እና ለማሰር እያዋሉት እንደሚገኙ” ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪው እነዚህ አዝማሚያዎች በአፍሪካ ብቻ የተገደቡ ባይሆኑም በአህጉሪቱ በእንደዚህ አይነት ህጎች ክስ የሚመሰረትባቸው ጋዜጠኞች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ ስለሪፖርቱ በሰጡት ማብራሪያ “እንደ ቡሩንዲ፣ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ያሉ ሀገራት ለህዝብ ደህንነት የታቀዱ ህጎችን የጋዜጠኝነት ስራን ወንጀል ለማድረግ እየተጠቀሙበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ለአብነት በናይጄሪያ አራት ጋዜጠኞች ከመንግስት ሙስና ጋር የተያያዘ ዘገባ ከሰሩ በኋላ በሳይበር ወንጀል ህግ ተከሰው በእስር ቤት እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
በእህጉሪቷ በዝርዝር ከተጠቀሱ ህጎች ባለፈ የተድበሰበሱ እና ስፋት ያላቸው ህጎች ጋዜጠኞችን ለማሰር እየዋሉም እንደሆነ ተነስቷል፡፡
ሲፒጄ የፀረ-መንግስት ህጎችን በመገናኛ ብዙሃን ላይ በማነጣጠር እና በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር በቀዳሚነት ባስቀመጣት ግብጽ 17 ጋዜጠኞች እስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ከፈረንጆቹ 2001 ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ጋዜጠኞችን በማሰር ተጠቃሽ የሆነችው ኤርትራ 16 ጋዜጠኞችን አስራለች፡፡
6 ጋዜጠኞች በእስር ላይ የሚገኙባት ኢትዮጵያ ከኤርትራ በመከተል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፤ ኢትዮጵያ ፣ ከካሜሩን፣ ሩዋንዳ እና ቱኒዚያ ጋር በመሆን በተራዘመ የፍርድ ሂደት ጋዜጠኞችን የሚያስሩ ሀገራ ናቸው ተብሏል፡፡