ሩሲያ በኩርስክ ግዛት በዩክሬን ከተያዘባት ቦታ ውስጥ 63 በመቶውን መልሳ መቆጣጠሯን አስታወቀች
ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ፈጣን በተባለ ግስጋሴ በምስራቅ ዩክሬን በርካታ መንደሮችን እየተቆጣጠረች ነው
ትራምፕ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ጋር ከወራት በፊት ፈረንሳይ ውስጥ የተገናኙ ሲሆን ከፑቲን ጋር በቅርቡ የስልክ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል
ሩሲያ በኩርስክ ግዛት በዩክሬን ከተያዘባት ቦታ ውስጥ 63 በመቶውን መልሳ መቆጣጠሯን አስታወቀች።
የሩሲያ ኃይሎች በምዕራብ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት በዩክሬን ኃይሎች ተይዞ ከነበረው ቦታ 63.2 በመቶ የሚሆነውን መልሰው መቆጣጠራቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒሰቴር በዛሬው እለት አስታውቋል።
ሮይተርስ ሚኒስቴሩ ሩሲያ በጥር ወር የመጀመሪያ ሁለት ሳምንት ውስጥ አራት መንደሮችን መልሳ ተቆጣጥራለች የሚለውን መረጃ ማረጋገጥ እንደማይችል ዘግቧል።
የዩክሬን ኃይሎች ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት የሩሲያን ድንበር ጥሰው በመግባት ሰፊ ቦታ መቆጣጠር የቻሉ ሲሆን ይህም ኪቭ ከሩሲያ ጋር ንግግር በምታደርግበት ወቅት የመደራደር አቅም ይፈጥርላታል ተብሏል።
ሶስት አመት ሊሞላው አንድ ወር ገደማ የቀረው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት አሁን የቀጠለ ሲሆን ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ፈጣን በተባለ ግስጋሴ በምስራቅ ዩክሬን በርካታ መንደሮችን እየተቆጣጠረች ነው።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል እቅድ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ትራምፕ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ጋር ከወራት በፊት ፈረንሳይ ውስጥ የተገናኙ ሲሆን ከፑቲን ጋር በቅርቡ የስልክ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።