የሪፐብሊካን ህግ አውጪዎች አሜሪካን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለማስወጣት እንቅስቃሴ ጀመሩ
“ተመድ አንባገነኖች የአሜሪካን እና አጋሮቿን የሚያጠቁበት መድረክ ሆኗል” ብለዋል ህግ አውጪዎቹ

ህግ አውጪዎቹ “ከዚህ አስመሳይ ድርጅት ልንወጣና ለዚህ ተቋም የምንከፍውን ክፍያ ማቆም አለብን” ብለዋል
የሪፐብሊካን ህግ አውጪዎች አሜሪካን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባልነት ለማስወጣት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገለጸ።
ህግ አውጪዎቹ ዓለም አቀፉ ድርጅት የአሜሪካን ጥቅም ማስቀደም አለመቻሉ እና ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “አሜሪካ ትቅደም” ፖሊሲ ጋር መጣጣም ባለመቻሉ ነው ለቆ የመውጣት ሀሳቡን ያቀረቡት።
ከሪፐብሊካን ህግ አውጪዎች መካል አንዱ የሆኑት ሴናተር ማይክ ሊ 2025 የተባለ ረቂቅ ህግ ያስተዋወቁ ሲሆን፤ ይህም አሜሪካ ከተመድ እና አጋር ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ለቃ እንድትወጣ እና የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ እንድታቋርጥ የሚያደርግ ነው።
ሌላኛው የሪፐብሊካን ሴናተር ቺፕ ሮይ፤ አዲሱ ረቂቅ ህግ ዛሬ ለምክር ቤት እንደሚቀርብ ገልጸው፤ የተመድ አካላት የአሜሪካን ጥቅም አያስቀድምም ብለዋል።
“ተመድ አንባገነኖች የአሜሪካን እና አጋሮቿን የሚያጠቁበት መድረክ ሆኗል” ብለዋል ሴናተር ቺፕ ሮይ።
"ስለዚህ ከዚህ አስመሳይ ድርጅት ልንወጣና ለዚህ ተቋም የምንከፍለውን ክፍያ ማቆም አለብን” ነው ያሉት ሴናተር ቺፕ።
“ፕሬዚደንት ትራምፕ አሜሪካን በማስቀደም የውጭ ፖሊሲያችንን እያሻሻሉ ነው፤ ሀገራችንን ሰላምና ብልጽግናን የሚጠብቅ እውነተኛ ጥምረትን ማስቀደም አለብን" ብለዋል።
አሜሪካ ከየትኛውም ሀገር በበለጠ ለተባበሩት መንግስታት የገንዘብ ድጋፍ ትሰጣለች የተባለ ሲሆን፤ በፈረንቹ 2022 ብቻ 18 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ እንደሰጠች መረጃ ያመለክታል።
አሜሪካ የምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ ከተመድ አጠቃላይ በጀት አንድ ሶስተኛውን ይሸፍናል ተበሏል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን እንደመጡ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ቀናቸው አሜሪካን ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት የሚያስወጣ ህግ መፈረማቸው ይታወሳል።